የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መዝሙር የሥነ-ጽሑፍ እና የዜማ ውበት ማሳያ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የተቋሙን ወታደራዊ ፍልስፍና፣ የሕገ-መንግሥት ታማኝነት እና ሀገርን የማስቀጠል ጥልቅ አደራ ያዘለ መመሪያ ነው።
ይህ ዜማ የሠራዊቱን ታሪካዊ ዳራ፣ የኅብረ-ብሔራዊነት ውበት እና የማይናወጥ የውጊያ ጽናት ከዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ ጋር ያዋሀደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።
የማንኛውም ጠንካራ ሠራዊት መሠረታዊ እሴት የሕዝብን ጥቅም ከራስ አስቀድሞ ማስቀመጥ ነው። በዚህ ረገድ የሠራዊታችን መዝሙር የሠራዊቱን አባላት አእምሯዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጁነት በጽናት በመቅረጽ በኩል ወደር የሌለው ሚና ይጫወታል።
ከመዝሙሩ ስንኞች ውስጥ የሠራዊቱን የማይበገር አቋም እና ፈተናዎችን በብቃት የማለፍ አቅም በግልጽ የሚያሳዩ በርካታ ጠንካራ ሀሳቦች ተሰድረው ይገኛሉ።
"ምድራዊ ፈተና በዝቶ ዙሪያው ቢነድ በገሞራ፣
ጥሰነው እናልፈዋለን የማይሞት ታሪክ ልንሠራ" የሚሉት ስንኞች ሠራዊቱ በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚያሳየውን የማይናወጥ ጽናት አጉልተው ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ሠራዊት በከባድ ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች እንዲሁም ውስብስብ ወታደራዊ ፈተናዎች በሚከበብበት ወቅት ወደኋላ የማያፈገፍግ እና የፈተናውን እሳት በጥሶ የማለፍ ተቋማዊ ጥንካሬ እንዳለው በተግባር አስመስክሯል።
"ወደ ትውልድ ተሻግሮ ወርሶት ፀንቷል እንደገና" የሚለው ሀሳብ ደግሞ የሠራዊቱ ጽናት ከየት እንደመጣ ይመልሳል። የዓድዋን፣ የካራማራን እና የሌሎች ታሪካዊ የዐርበኝነት እሴቶችን ከአሁኑ ዘመናዊ ኃይል ጋር በማያያዝ የመጽናት መንፈስ ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑን ያውጃል።
የሠራዊታችን ጽናት የሚመነጨው ከዘመናዊ ትጥቅ እና ከቴክኖሎጂ ልዕልና ብቻ ሳይሆን፣ ትልቁ የጽናት ምንጭ ሕዝባዊ ደጀንነቱ ነው።
"ሕዝብ ነው ኃያል ክንዳችን፣ ሰላም ልማት ነው ቋንቋችን" በሚለው ሐረግ ውስጥ፣ ሠራዊቱ ከሕዝብ ማኅፀን የወጣ የሰላም ዘብ መሆኑን ይነግረናል። ሆኖም ይህ የሰላም ፍላጎት ከከፍተኛ ወታደራዊ የማስጠንቀቅ እና የመከላከል አቅም ጋር የተቆራኘ ነው።
"የማንጨበጥ ነበልባል እሳት ነን ለጠላታችን፣
ፍሙ ከርቀት ይፋጃል ብረት ያቀልጣል ክንዳችን" የሚለው የዜማ ክፍል የጠላትን ጥቃት በሩቅ የማክሸፍ እና ለማንኛውም ወረራ የማይበገር ኃይል የመገንባትን ስትራቴጂካዊ ከፍታ ያሳያል።
የሠራዊቱ ጽናት በሰላም ጊዜ በሕዝባዊ ወገንተኝነቱ፣ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ብረት በሚያቀልጠው ተጋድሎው ይገለጻል።
"በደም ዐሻራሽ አትመው ሕዝቦች ለሰጡን አደራ" የሚለው ዐቢይ ሀሳብ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በሠራዊቱ መካከል ያለውን የማይበጠስ የማኅበራዊ ውል ያመላክታል።
ይህንን አደራ ለመጠበቅ ሠራዊቱ የሚከፍለውን ዋጋ ሲያትት ፦
"ኢትዮጵያ በእኛ ደም ደምቃ በአፅማችን ፍላፅ ተማግራ፣
እንደታፈረች እንድትኖር ከዘመን ዘመን ተከብራ፣
ከመሞት በላይ እንሙት ደማችን ሺህ ጊዜ ይፍሰስ" ይላል።
"በአፅማችን ፍላፅ ተማግራ" የሚለው ዘይቤ፣ የሀገር ህልውና ቀጥሎ የሚኖረው በሠራዊቱ አጥንት እና ደም መሠረትነት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
"ከመሞት በላይ እንሙት" የሚለው አገላለጽ ደግሞ፣ የላቀ የመስዋዕትነትን እና የማይናወጥ ጽናትን የመጨረሻ ጥግ ይገልጻል።
መሞት ተፈጥሯዊ ግዴታ ቢሆንም፣ "ከመሞት በላይ መሞት" ግን ለዓላማ እና ለሀገር ፍቅር ሲባል በሙሉ ፈቃደኝነት የሚከፈል የጀግኖች ክብር ነው።
የመከላከያ ሠራዊታችን መዝሙር እግረኛው በምድር ወሰን፣ አየር ኃይሉ በሰማይ ዘብነት፣ ኮማንዶው በጥብቅ ዲሲፕሊን፣ እንዲሁም ሜካናይዝድ እና ሌሎች ክፍሎች በቴክኖሎጂ አቅማቸው የሚያሳዩትን ተግባራዊ ጽናት የሚገልጥ ሕያው መሐላ ነው።
መዝሙሩ ሠራዊቱ የሕገ-መንግሥቱን እና የሕዝቦችን ዘላለማዊ ህልውና በደም እና በአጥንቱ የመጠበቅ አቋሙን ለዓለም የሚያበስርበት የዜማ ዶክትሪን ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: