አረንጓዴው ወርቅ በመባል የሚታወቀው እና በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው የአቮካዶ ምርት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ከፍታ ከሚያበስሩ አዳዲስ ስትራቴጂያዊ ምዕራፎች አንዱ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት በስፋት በተተገበረው የሃስ አቮካዶ ልማት በሲዳማ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በስፋት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምረዋል።
የቀዝቃዛ ባቡር ኮንቴነር መሠረተ ልማትን በመጠቀም ወደ አውሮፓ ገበያ የሚደረገው ኤክስፖርት ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት በዓለማችን ቀዳሚ ከሆኑ የአቮካዶ አምራች እና ላኪዎች ተርታ ለመሰለፍ የሚያስችላትን ግዙፍ ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ይፋ አድርጋ ወደ ሥራ ገብታለች።
ለዚህ ታላቅ የልማት ምዕራፍ 38.5 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የግብርና መዋቅር ወደ ዘመናዊና ኤክስፖርት መር ምህዳር የሚያሸጋግር ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
ይህ ኢኒሼቲቭ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ ባለፈ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ለመለወጥ ያለመ ነው።
በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው የሃስ አቮካዶ ዝርያ በኪሎ ግራም እስከ 7 የአሜሪካ ዶላር የሚሸጥ ሲሆን፣ አጠቃላይ ዓለም አቀፉ የአቮካዶ ገበያም ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ የንግድ አውታር ነው።
ኢትዮጵያ ካላት ተስማሚ የከፍታ መጠን፣ ለም መሬት እና ምቹ የአየር ንብረት አንጻር ከዚህ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚገባትን ድርሻ ለመውሰድ ሰፊ አቅም አላት።
በኢኒሼቲፉ የአቮካዶ ልማት ሽፋንን ከነበረበት 100 ሺህ ሄክታር ወደ 191 ሺህ ሄክታር ማሳደግ እንዲሁም ዓመታዊ የምርት መጠንን ከ400 ሺህ ቶን ወደ 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
ይህም የምርት መጠኑን በዘጠኝ እጥፍ ገደማ የሚያሳድግ ሲሆን፣ ከ3 ሚሊዮን በላይ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን የኢኮኖሚ አቅም በመገንባት የዘላቂ ብልጽግና ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል።
በተጨማሪም አርሶ አደሩ ዘመናዊ የምርት አያያዝ፣ የጥራት ቁጥጥር እና የድህረ-ምርት ብክነትን የመቀነስ ሥልጠናዎችን እንዲያገኝ ድጋፍ ይደረጋል።
በመሠረተ ልማት በኩል የሚገነቡት የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፓርኮች እና የቅዝቃዜ ሰንሰለት አቅርቦቶች ምርቱ ሳይበላሽ ለዓለም አቀፍ ገበያ በወቅቱ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
አቮካዶ አሁን ላይ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ለትላልቅ አግሮ-ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች የጥሬ እቃ ግብዓት በመሆን የኢንዱስትሪ እና የግብርና ትስስርን ያጠናክራል።
በስፋት ወደ ውጭ ገበያ በመቅረብም ብሔራዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደጉ ባሻገር የንግድ ሚዛንን በማስተካከል ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: