በተቋማት ደረጃ የሚከናወኑ የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን የማጠናከር ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ጎዴ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ አቅመ-ደካማ ወገኖች ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ከሙሉ የቤት ዕቃዎቻቸው ጋር ዛሬ አስረክቧል።
ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው እነዚህ ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ሲሆን፣ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብተው መጠጠናቀቃቸው ተገልጿል።
አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ቤቶቹን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሀገር ልማት እና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማገልገሉ ባለፈ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን እና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መንግሥት ለሚያከናውናቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ትልቅ ማሳያ ነው።
በክረምት ወራት በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ፣ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ቤተሰቦች ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት እንዲሁም የአቅመ-ደካሞችን ቤት ማደስ እና መገንባት በስፋት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አፈጉባኤው አስታውሰዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ባለፉት ስድስት ዓመታት እነዚህን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተጠናከረ መንገድ ሲያከናውን መቆየቱን አብራርተዋል።
ቤቶቹን የተረከቡት ወገኖች በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ከዝናብ እና ከፀሐይ በማይከላከል ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ገልጸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: