በኢትዮጵያ ሊከሰቱ የሚችሉ የአየር ሁኔታዎችን አስቀድሞ በመገንዘብ ተገቢውን ዝግጅት እና የምላሽ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ወቅት ትንበያ ግምገማ እና የበጋ ወቅት ትንበያ ይፋ የሚያደርግበት መድረክ በአዳማ ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፣ በክረምት ወቅት የነበረው የዝናብ ስርጭት እና ተፅዕኖ ኢንስቲትዩቱ አስቀድሞ ከሰጠው ትንበያ ጋር ተመሳሳይነት ነበረው። ይህም ኢንስቲትዩቱ ትክክለኛ እና አስተማማኝ ትንበያዎችን በመስጠት ረገድ ያለውን አቅም እያሳደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ፣ የኢንስቲትዩቱ የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ 79 በመቶ ልክ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ክረምት ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ዋናው የዝናብ ወቅት ሆኖ፣ ከዓመታዊ የዝናብ ድርሻ እስከ 85 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍን የተጠቆመ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የነበረው የዝናብ ሁኔታ ለግብርና እና ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ምቹ እንደነበር ተገልጿል።
የበጋ ወቅትም አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል ደረቅ፣ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ጠባይ የሚያደርግ ቢሆንም፣ በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ የሀገራችን ክፍሎች ግን ይህ ወቅት ሁለተኛው የዝናብ ወቅት መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኘው የበጋ ዝናብ ከዓመታዊ የዝናብ ድርሻቸው እስከ 45 በመቶ ይሸፍናል። ከዚህ በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተወሰኑ አካባቢዎች የመኸር ዝናብ እስከ ኅዳር ወር ድረስ እንደሚቀጥል የትንበያ መረጃው ያመለክታል ተብሏል።
በመደበኛ ሁኔታ የበጋ ወቅት የዝናብ ተጠቃሚ ያልሆኑት የሰሜን፣ መካከለኛ፣ ምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ከጥር ወር ጀምሮ አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ኢንስቲትዩቱ በትንበያው ተመላክቷል።
በበጋ የሚገኘውን የዝናብ መጠን እና ስርጭት በአግባቡ መጠቀም እንደሚባ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በአባዲ ወይናይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: