Search

ማሽቃሮ፤ የካፊቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል

ሓሙስ መስከረም 07, 2019 56

ኢትዮጵያ በብዝኃ ባህል፣ በቋንቋ፣ በታሪክ እና በባህላዊ እሴቶች የበለጸገች ሀገር ናት።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከበሩ ባህላዊ በዓላት የሕዝቦችን የአኗኗር ዘይቤ፣ የታሪክ ትውስታ፣ የዕሴት ሥርዓት እና የማኅበራዊ ትስስር የሚያሳዩ ሕያው ቅርሶች ናቸው።

ከእነዚህ ባህላዊ በዓላት መካከል የካፋ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው "ማሽቃሮ" ተጠቃሽ ነው።

ማሽቃሮ የካፊቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫን ለማስታወስ፣ ያለፈውን ዘመን ለመሰናበት እና አዲሱን ዘመን በተስፋ እንዲሁም በመልካም ምኞት ለመቀበል የሚከበር በዓል ነው።

ማሽቃሮ በካፋዎች ዘንድ የአዲስ ዘመን መግቢያን ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን፣ የካፋ ሕዝብ የጋራ ማንነት፣ ባህላዊ እሴት እና ማኅበራዊ ትስስር የሚገለጽበት ልዩ የባህል መድረክ ነው።

ማሽቃሮ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ፣ በባህላዊ ጥበብ፣ በትውፊት እና በተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶች ውስጥ ተጠብቆ የቆየ ሲሆን፣ ከዚሁ ሰፊ የባህል ሥርዓት የሚመነጭ የካፋ ሕዝብ በዓል ነው።

ማሽቃሮ የካፋን ሕዝብ ታሪክ፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የፍቅር እና የአንድነት እሴቶችን በውስጡ ይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የዘለቀ እና በካፋዎች ዘንድ ጠንካራ መሠረት ይዞ ለቆየው ማኅበራዊ መስተጋብር ሁነኛ መተማመኛ ነው።

ማሽቃሮ ሲከበር በተለያዩ ባህላዊ መገለጫዎች ደምቆ ይውላል፡፡ ሕፃን አዋቂው በባህላዊ ልብስ ያሸበርቃል፤ የማይጠገበው የካፊቾ ባህላዊ ዘፈን እና ጭፈራም ይደምቃል።

በካፊኛ " ማኖና" (እህቴ፣ ወንድሜ) እየተባባሉ ባህላዊ ምግባቸውን፣ መጠጣቸውን እንዲሁም "የማኪራ" ቡናቸውን በጋራ እየጠጡ መልካም ምኞታቸውን ይለዋወጣሉ።

በዓሉ ሲደርስ በሚዘጋጁ ባህላዊ የእጅ ሥራዎች፣ ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ ልብሶች፣ ለበዓሉ በሚቀርቡ የደለቡ ሠንጋዎች፣ በዓይነቱ ልዩ በሆነው የካፋ በግ፣ ተፈጥሮ ከቸረቻቸው ጫካ በሚገኙ ቅመማ ቅመሞች እና በሌሎች የአካባቢው ምርቶች ገበያው ይደራል።

ይህም በካፋዎች ዘንድ ለዘመናት ተሰናስሎ የቆየውን ባህል ከኢኮኖሚ ጋር የማገናኘት ጥበባቸውን ያመላክታል።

ካፋ በተፈጥሮ እና በባህል ሀብቱ የተለየ የቱሪዝም አቅም ያለው አካባቢ ነው። ማሽቃሮም ከእነዚሁ ሀብቶች ጋር ይበልጥ እየዳበረ የመጣ በዓል ሲሆን፣ የዞኑ የቱሪዝም አቅም በዓለም ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲታይ ዓይነተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ የሚገኝ የካፊቾዎች መገለጫ ነው።

የዘንድሮው ማሽቃሮ ለዘመናት በትውልድ ተጠብቆ በቆየው የካፋ ንጉሥ መናገሻ "ቦንጊ ሸምበቶ" የብሔሩ ተወላጆች በተገኙበት፣ እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች የተጋበዙ እንግዶች በሚታደሙበት የተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ መስከረም 12 በድምቀት ይከበራል።

በሰለሞን ባረና

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: