"መልሕቅ አርማዬ
ቀይ ባሕር ቤቴ፤
ጀግንነትም ውርሴ
የአባት የአያቴ" …
በሚለው ተወዳጅ እና ግርማ ሞገስ ባለው ስንኝ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መዝሙር ከዜማነት ያለፈ ጥልቅ ትርጉም አለው።
ይህ ስንኝ የኢትዮጵያን የባሕር ታሪክ፣ ጂኦፖለቲካዊ ማንነት እና ታሪካዊ እውነት አቅፎ የያዘ ተቋማዊ እና ብሔራዊ መግለጫ ነው።
በባሕር ኃይሉ የሥልጣኔ እና የጥንካሬ ዘመናት የተደረሰውን ይህን መዝሙር ሥነ-ልቦናዊ እና ስትራቴጂያዊ ይዘት ስንመረምረው፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ዳራ ከወቅቱ የባሕር በር ጥያቄ ጋር የሚያያይዙ በርካታ ምሳሌያዊ እውነታዎችን እናገኛለን።
በመዝሙሩ መግቢያ ላይ የሚገኘው "መልሕቅ" የጽናት፣ የዕውቅና እና የወደብ ባለቤትነት ቋሚ ምልክት ሲሆን፣ "ቀይ ባሕር ቤቴ" የሚለው ሐረግ ደግሞ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና የነበራትን ታሪካዊ እና መልክዓ ምድራዊ ባለቤትነት ያጎላል።
ይህ ሐረግ ባሕርን እንደ ውጫዊ ጉርብትና ሳይሆን እንደ ተፈጥሯዊ መኖሪያ የመቁጠር ጥልቅ ሥነ-ልቦናዊ ዕይታን ያንፀባርቃል።
"ጀግንነትም ውርሴ፣ የአባት የአያቴ" የሚለው ስንኝ ደግሞ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለዘመናት የባሕር ዳርቻዎቿን ስታስከብር የቆየችበትን የትውልድ ቅብብሎሽ እና የፍቅር መሥዋዕትነት በግልጽ ያመላክታል።
ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቀይ ባሕር ዳርቻን ለማስጠበቅ እና የዓለም አቀፍ ንግድ መስመር ደኅንነትን ለማረጋገጥ በ1948 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታዊ ባሕር ኃይልን መሠረቱ።
በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ይህ ኃይል ታላላቅ የዓለም ኃያላን መንግሥታት በሥልጠና እና በቁሳቁስ ድጋፍ ያደረጉለት ዘመናዊ ተቋም ለመሆን በቅቶ ነበር።
በ1980ዎቹ ማጠቃለያ ላይ ደግሞ ከ11 ሺህ 500 በላይ አባላት እና ከ81 በላይ የተለያዩ የጦር እና የጥበቃ መርከቦችን በማደራጀት በምሥራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባሕር ቀጣና ገዥ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ኃይል ሆኖ አገልግሏል።
የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ሤራ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የቀይ ባሕር በሮቿን አጥታ በ1988 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በይፋ እንዲፈርስ ተደረገ።
ይህ በአሻጥር የተፈጠረው ክስተት ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ባሕሯ በመለየት የሎጂስቲክስ እና የደኅንነት ጥገኝነት ዳረጋት።
ኢትዮጵያ ከባሕር ርቃ በቆየችባቸው ሦስት ዐሥርተ ዓመታት ይህ መዝሙር በሕዝቡ እና በወታደራዊው ማኅበረሰብ ልቦና ውስጥ የማይጠፋ የቁጭት ረመጥ ሆኖ ቆይቷል።
መዝሙሩ ታሪክን እያስታወሰ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በይፋ እስከተነሣበት አሁናዊ ወቅት ድረስ ትውልድን ከባሕር ጋር የሚያያይዝ ጠንካራ ሥነ-ልቦናዊ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል።
ከ2010 ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ የተመዘገበውን ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ለውጥ ተከትሎ መንግሥት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይልን እንደ አዲስ አደራጅቷል።
ይህ ውሳኔ በቀጣናው እየተቀያየረ የመጣውን የጂኦፖለቲካ ውጥረት፣ የባብ ኤል-መንደብን ስትራቴጂያዊ አስፈላጊነት እንዲሁም የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ ብሔራዊ ደኅንነት ያገናዘበ ወቅታዊ እርምጃ ነው።
በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን ቀይ ባሕር የዓለም አቀፍ ንግድ ማስተላለፊያ እና የኃያላን ፉክክር ማዕከል መሆኑ የባሕር ኃይሉን ዳግም ምሥረታ እጅግ አስፈላጊ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቀይ ባሕር ቀጣና እየተፈጠረ ያለውን ሁኔታ እንደ ብሔራዊ የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ተግዳሮት ትመለከታለች።
ይህንን ፈተና ለመሻገር እና በሰላማዊ ዲፕሎማሲ አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን ከፍተኛ ሀገራዊ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
የመዝሙሩ ስንኞች ትላንት የነበረውን የባሕር ግርማ እያስታወሱ ለዛሬው የባሕር በር ጥያቄ ሥነ-ልቦናዊ ስንቅ በመሆን፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ ቀጣና የነበራትን የላቀ ድርሻ እንድትመልስ የሚያስገነዝብ የትውልድ አደራ ማሳያ ሆነው ይቀጥላሉ።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: