Search

“ጂኦግራፊ የሀገራትን ዕጣ ፋንታ ሊወስን አይገባም” - የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን

ዓርብ ነሐሴ 09, 2017 108

ጠንካራ ሀገር በመገንባት በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሷ ሚና ያላት ሀገር መሆን የኢትዮጵያ አንዱ የውጭ ጉዳይ አቅጣጫ ነው፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ደግሞ የዕቅዱ አካል ነው።

ይህን እሳቤ በማንገብ በቱርኬሚስታን አዋዛ ከተማ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት 3ኛው የባሕር በር የሌላቸው አዳጊ ሀገራት ጉባኤ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ፍሬያማ ቆይታ እንደነበረው በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ተናግረዋል።

“ጂኦግራፊ የሀገራትን ዕጣ ፋንታ ሊወስን አይገባውም” የሚለው የኢትዮጵያ አቋምም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተጠናከረበት መሆኑን አንሥተዋል።

በማደግ ላይ ያሉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እየቀነሰ የመጣበት፣ የወጪ ንግዳቸው የባህር በር ካላቸው ሀገራት ጋር ሲነጻጸር 18 በመቶ ዝቅ ያለበት፣ የሰው ኃይል ልማታቸው በ19 በመቶ ያነሰበት እና ለመሰል የዕድገት ማነቆ መጋለጣቸውን ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ጉባኤው እነዚህን ችግሮች መፍታት ላይ መምከሩንም ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በታሪክ የባህር በር የነበራት ኢትዮጵያ ከአማራጩ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቷ ከሌሎቹ ሀገራት እንደሚለያት ተናግረዋል።

የጋራ የውኃ ሀብቶች የዓለም ሕዝብ ንብረት በመሆናቸው ሁሉም ሀገር ያልተገደበ የመጠቀም መብት እንዳለው አስታውሰዋል።

ከዚህም ባሻገር አስተማማኝ ኮሪደር የማግኘት፣ በባህር ላይ ያሉ ሀብቶችን የመጠቀም ብሎም ጥናት እና ምርምር ለማካሄድ የሚሉ ሐሳቦች በጉባኤው ላይ መነሳታቸውን ገልጸዋል።

“በዚህም ኢትዮጵያን ወክለን ይዘነው የሄድነው ጥያቄን ያስመለስንበት ለማለት የሚያስችል ተሳትፎ ነበረን” ያሉት ዶ/ር ፈትሂ፣ ኢትዮጵያ አጋሮች ያበጀችበት የአዋዛ ቆይታ የልማት ፍላጎቷን ከፖሊሲዋ ጋር አጣጥማ እንድትተገብር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ጥያቄያችን ተመልሷል ለማለት የሚያስችለው የቱርኬሚስታን ቆይታችን እሙን እንዲሆን ሰላም እና አንድነታችንን ልናስጠብቅ ይገባናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአፎሚያ ክበበው

#EBC #ebcdotstream #accesstothesea #LLDC3 #RedSea