Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለሌሎች ወደብ አልባ ሀገራት ጭምር በር ከፋች ሆኗል

ዓርብ ነሐሴ 09, 2017 112

ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ላይ ትገኛለች ያሉት የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ፤ ጥያቄዋም ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን አክለዋል።

ፕሮፌሰር ብሩክ ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የሀገሪቱ የባሕር በር ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘት የቻለው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የቀረበ በመሆኑ ነው ብለዋል።

መንግሥት እና ህዝብ እንዲናበቡ የተከናወነው ውጤታማ ሥራም ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የተናገሩት።

ከባሕር በር ጥያቄው ጋር በተያያዘ መጀመሪያ ላይ ግርታ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ መጥራቱን እና በተለያዩ ሀገራት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ወደብ አልባ ሀገራት ጭምር በር ከፋች የሆነ ጥያቄ ማንሳቷን ነው የተናገሩት።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በቅርቡ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዞ ግማሽ መንገድ ተራምዷል ማለታቸውም ጥያቄው ተቀባይነት እያገኘ ስለመምጣቱ አመላካች ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ብሩክ።

በንፍታሌም እግዳወርቅ

#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #ኢትዮጵያ #የባሕርበር