Search

የቦረናን የድርቅ ታሪክ የሚቀይር አዲስ የልማት ስትራቴጂ እውን ሆኗል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ዓርብ ሐምሌ 03, 2018 93

የቦረናን ማኅበረሰብ ለረጅም ዘመን ሲፈትን የቆየውን የውኃ እጥረትና የድርቅ ታሪክ ለመቀየር፣ ተፈጥሮን ማኅበረሰቡን በሚያገለግል መልኩ የመምራት አዲስ ስትራቴጂካዊ ሥርዓት በስኬት እየተተገበረ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት ፅሁፍ፤ እውነተኛ ልማት ማኅበረሰቡን በሚያገለግል መልኩ ማስተዳደር መሆኑን ጠቅሰው፣ በቦረና የነበረው የውኃ እጥረት የአገልግሎት ችግር ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሕይወት ሥርዓት፣ የምርታማነትና የወደፊት ተስፋ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ፕሮጀክቶች ስልታዊ አመለካከት በመዘንጋታቸው፣ አካባቢውን ያላገናዘቡ ቴክኖሎጂዎች በጥቅም ላይ በመዋላቸውና የተቋማት ቅንጅት ባለመኖሩ የተፈለገውን ዘላቂ ውጤት ሳያመጡ መቅረታቸውን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት የቦረናን አካባቢ የውሃ  ችግር ከመሠረቱ ለመቅረፍ የውኃ ጉድጓድ ከመቆፈር ባለፈ፣ እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ ሁለት ዋና ዋና ምሰሶዎችን ያገናኘ ወጥ ሥርዓት መዘርጋቱን አቶ ሽመልስ አብራርተዋል፡፡

ይህ የተዘረጋው ስርዓት የአፈር ጥበቃን፣ የችግኝ ተከላና እንክብካቤን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን እንዲሁም የተፋሰስ ልማትን ያካተተ ሲሆን፤ ዋና ግቡ የአፈርን የማምረት አቅም ጠብቆ ውኃን አቁሮ እንዲይዝ ማድረግ ነው።

የዝናብና የጎርፍ ውኃን መቆጣጠር፣ የከርሰ ምድር ውኃ ክምችትን ማጠናከር እና የውኃ ተፋሰስን በሚያስፈልግበት ጊዜና ቦታ በመቀየር አጠቃላይ የውኃ ዑደትን ማስተዳደርን ያካትታል።

አዲሱ የቦረና ውኃ ፕሮጀክት የዚህ ስትራቴጂካዊ ፍልስፍና ውጤት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ጥናቶች ተካሂደው፣ ዲዛይኖች ተሻሽለውና ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ውለው ዘመናዊ አሠራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

ዛሬ ላይ የውኃ ጉድጓዶች፣ የፓምፕ ጣቢያዎች፣ የውኃ ማጠራቀሚያዎችና በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠሩ የውኃ ቧንቧዎች እርስ በርስ በተገናኘ አንድ ወጥ ሥርዓት ውስጥ እየሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

ትልቁ ስኬት የቧንቧው ርዝመት ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት ከተራ ፕሮጀክት ግንባታ ባለፈ ዘላቂ ሥርዓት መገንባት መቻሉ ነው ብለዋል።

የማኅበረሰቡን አገር በቀል የውኃ ማቆር ባህል በዘመናዊ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በማጠናከር በአሁኑ ወቅት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው፤ 23 የፊና ግድቦች እና 234 የማኅበረሰብና የቤተሰብ ኩሬዎች  መቆፈራቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ ሥራዎች በበጋ ወቅት ውኃ እንዲገኝ፣ በክረምት ደግሞ ጎርፍን ለመቆጣጠርና የውኃ ሀብቱ መጪውን ትውልድ እንዲያገለግል ለማድረግ ታላቅ አቅም መፍጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡

የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ውኃ የእንስሳት እርባታን የሚያጠናክር፣ ግብርናን የሚያስፋፋ፣ ኢንቨስትመንትን የሚስብ እና የሥራ ዕድል የሚፈጥር የምርታማነት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

 

በሀይማኖት ከበደ