Search

ከቋንቋ ዲጂታላይዜሽን እስከ ዓለም አቀፍ እውቅና፤ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጉዞ

ዓርብ ሐምሌ 03, 2018 93

አንድን ሀገር ያለ ባሕልና ኪነ ጥበብ ማሰብ፣ ነፍስ የሌላትን ሥጋ እንደመመልከት ነው። የዲጂታል ዘመን ቴክኖሎጂዎች የባሕል እሴቶችን በምናባዊ ዓለም እያደመቁ የማይዳሰሱ ቅርሶች ደግሞ በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ገናናነት በሚያስመሰክሩበት በዚህ የታሪክ ምዕራፍ፤ ጥበብ ከግል ስሜት መግለጫነት ተሻግራ የሀገር መካሻና የሕዝቦች ትስስር ዋነኛ መገለጫ ሆናለች። 

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የባሕልና ኪነ ጥበብ ዘርፍ የታየው ለውጥ ሀገራዊ አንድነትንና ማኅበራዊ እሴትን በአዲስ መልክ የመቅረጽ ጥልቅ ስትራቴጂካዊ ምዕራፍ ነው።

ኢትዮጵያ የብዙኃነትና የደመቁ ባሕላዊ ፀጋዎች ምድር መሆኗ ቢታወቅም እነዚህን እሴቶች ወደ ወል ትርክትና ወደ ጠነከረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመቀየር ሥራ ግን የአደባባይ ጥበብን በሕግና በመሠረተ ልማት ማዕቀፍ መደገፍን ይጠይቅ ነበር።

ጥበብ ለውበት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ግንባታ መድህን ናት የሚለው እምነት ባለፉት አምስት ዓመታት በተግባር የተፈተነ እውነት ሆኗል። ይህ ዘርፍ ከውበት ማድነቂያነት ተሻግሮ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር ዋነኛ ምሰሶ እንዲሆን የተደረገው ሥር ነቀል ጉዞ፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ገጽታ ቀይሮታል።

ይህንን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ከተከናወኑት ቁልፍ ተግባራት መካከል የጥበባት፣ የፊልም፣ የቋንቋና የባሕል ረቂቅ ፖሊሲዎች ተዘጋጅተው ሕጋዊ መሠረት እንዲይዙ መደረጉ ግንባር ቀደሙ ነው። እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች የብዝኃነትን ውበት ወደ አንድ የጋራ ጥንካሬ የሚቀይሩ እንጂ አንዱን አግልለው ሌላውን የሚያነግሡ አይደሉም።

በተለይም የቋንቋ ፖሊሲው ብሔሮችና ብሔረሰቦች በማንነታቸው እንዲኮሩና ቋንቋቸውን ለትምህርትና ለዕለታዊ አገልግሎት እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህንኑ መሠረት በማድረግ ከ30 በላይ ቋንቋዎች ዲጂታላይዝድ መደረጋቸው ደግሞ ዜጎች የሌላውን ማኅበረሰብ ቋንቋ በቀላሉ እንዲማሩና የእህትማማችነትና ወንድማማችነት ዕሴት በተግባር እንዲጎለብት አድርጓል።

ከሀገራችን ጫፍ እስከ ጫፍ ከሚገኙ ከ54 ሺህ በላይ ከያንያን ጋር የተደረገው ሰፊ ውይይትም ባለሙያዎች ጥበባቸውን ለብሔራዊ ጥቅም፣ ለአብሮነትና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እንዲያውሉ አዲስ የሞራልና የሙያ መነቃቃትን ፈጥሯል።

የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ ለትውልድ ለማሻገርና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ቦታ ከፍ ለማድረግ በቅርስ ጥበቃና እውቅና ረገድ የተመዘገቡት ድሎችም ታሪካዊ ናቸው። የጊፋታ፣ የፊቼ ጨምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ የመስቀል፣ የጥምቀትና የሸዋሊድ በዓላት በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገባቸው የኢትዮጵያን ብዝኃነት የዓለም ቅርስ አካል አድርጎታል።

ከዚህ ጎን ለጎን ለዘመናት ጥገና ሳይደረግላቸው የፈረሱና የተረሱ ከ28 በላይ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች በከፍተኛ በጀት ታድሰው ለዕይታ መብቃታቸው ያለፈውን ታሪክ የማክበርና የማደስ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው። እነዚህ ቅርሶች ዛሬ የቱሪስት መናኸሪያ ብቻ ሳይሆኑ የጋራ ማንነታችን መለኪያዎች ሆነዋል።

የባሕልና ኪነ ጥበብ ልማቱ በፖሊሲና በቅርስ ጥበቃ ብቻ ሳይገደብ የከተሞችን ገጽታና የማኅበረሰቡን የኑሮ ዘይቤ በለወጡት የገበታ ለሀገርና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የኪነ ጥበብ ማዘውተሪያዎች ዋነኛ አካል እንዲሆኑ ተደርገዋል።

በዚህም መሠረት በመላ ሀገራችን የተገነቡት 53 አንፊ ቴአትሮች፣ 39 ሲኒማ ቤቶችና 110 ፕላዛዎች የሕዝብ መገናኛ፣ የባሕል ልውውጥና የኪነ ጥበብ ማዕከላት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

የሀገርን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የተደረገው የ"ኪን-ኢትዮጵያ" የባሕልና ጥበባት ጉዞም የኢትዮጵያን እውነተኛ የሰላምና የብልጽግና ገጽታ ለዓለም ያስመሰከረ ነበር።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሀገራቸው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጥበብ ባለውለታዎች የመታሰቢያ ሐውልቶች በአዲስ አበባ መቆማቸውና ተገቢው ክብር መሰጠቱ ዘርፉን ወደ ላቀ ክብር ያሸጋገረ ተግባር ሆኗል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑት የባሕልና ኪነ ጥበብ ሥራዎች ኢትዮጵያ ያላትን ሁለንተናዊ ብዝኃነት እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ትልቅ ውበትና ጥንካሬ እንድትጠቀምበት አስችለዋል።

በጥበብ የተገነባችና እሴቶቿን የጠበቀች የበለፀገች ሀገርን ዕውን ለማድረግ የተጣለው መሠረት ዛሬ ለምናየው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ማኅበራዊ ትስስር ዋነኛ ዋስትና ሆኗል። ይህ በስትራቴጂካዊ መንገድ የተጀመረው አኩሪ የልማት ጉዞ ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ የሚተርፍ ታላቅ ሀገራዊ አሻራ ነው።

በበረከት ሽመልስ