የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዲስ ያለማውን ‘Government Digital Office Platform /GDOP/’ የተሰኘ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የመንግሥት ዲጂታል ኦፊስ ፕላትፎርም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ አስመርቋል።
‘GDOP’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ቴክኖሎጂው በውስጡም የወጪ ገቢ ደብዳቤ ማኔጅመንት ሲስተም፣ የጎብኚዎች ማኔጅመንት ሲስተም፣ የትራንስፖርት ማኔጅመንት ሲስተም የያዘ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የደንበኞች ማኔጅመንት ሲስተም፣ የግንባታ ፍቃድ አገልግሎት እና ሪሶርስ ማኔጅመንት ሲስተምን፣ የዕቅድ እና ቁጥጥር ማኔጅመንት ሲስተምንም ያካተተ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
በቴክኖሎጂው የ‘ኢ ሰርቪስ ፖርታል’ አገልግሎቱም ተሻሽሎ መቅረቡ የተገለጸ ሲሆን ዛሬ የተመረቀው ዲጂታል አገልግሎቱ ደንበኞችን ከእንግልት ነፃ የሚያደርግ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መሆኑም ተገልጿል።
ከተገልጋዮች ባሻገርም የተቋም ሠራተኞችም በርካታ ተገልጋዮችን በአጭር ጊዜ እንዲያስተናግዱ ከማስቻሉም ባሻገር ግልጽነት የተላበሰ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ተብሏል።
በሳምሶን በላይ