እ.አ.አ ከ2000 ጀምሮ ባሉት ዓመታት ሩሲያን በፕሬዚዳንትነት የመሩት እና እየመሩ የሚገኙት ቭላድሚር ፑቲን እስካሁን ከአምስት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ጋር 48 ውይይቶችን አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከአምስቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ጋር በቡድን 8፣ ቡድን 20፣ በተባበሩት መንግሥታት፣ የእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር፣ በኔቶ ጉባኤዎች እና በሁለቱ ሀገራት የጋራ ውይይትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
እ.አ.አ ማርች 26 ቀን 2000 ሩሲያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቦሪስ ዬልሲንን ሥልጣን መልቀቅ ተከትሎ አዲሱ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ።
ከወራት በኋላም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቢል ክሊንተንን በክሬምሊን ተቀብለው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።

ቀጥሎም የቢል ክሊንተን የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ የወራት ዕድሜ ብቻ በቀረበት ወቅት በቡድን 8 (G8) ጉባኤ ላይ በጃፓኗ ኦኪናዋ ከተማ መገናኘት ችለው ነበር።
በኒው ዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ፣ ከዚያም በብሩናይ በተካሄደው የእስያ ፓስፊክ ሀገራት የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይም ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ከአሜሪካው አቻቸው ጋር ካደረጓቸው ውይይቶች በአንዱ ሩሲያ የኔቶ አባል እንድትሆን ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ፕሬዚዳንት ክሊንተንም መጀመሪያ አካባቢ “አዎ፤ ይቻላል” ብለው እንደመለሱላቸው እና በኋላ ላይ ግን “አይሆንም” እንዳሏቸው በአንድ ወቅት ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ተናግረው ነበር።
በዚህ መልኩ የተጀመረው የፑቲን እና የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ውይይት ቀጥሎ ፑቲን ከቢል ክሊንተን በኋላ አሜሪካን ለመምራት ከተመረጡት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ጋር በጁን 16 ቀን 2001 ስሎቬንያ ውስጥ ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በዚህ የተጀመረው የቭላድሚር ፑቲን እና የጆርጅ ቡሽ ውይይት ጆርጅ ቡሽ በድጋሚ ተመርጠው በኋይት ሐውስ በቆዩባቸው ከ2001-2008 ባሉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ለ28 ጊዜያት ተገናኝተው በኑክሌር የጦር መሣሪያዎች ቅነሳ፣ በኔቶ ጉዳዮች፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው አለመግባባት ዙሪያ እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በእነዚህ በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ መሪዎች መካከል ለ28 ጊዜያት ተደርገው ከነበሩ ውይይቶች ውስጥም አንዳንዶች በመግባባት እና በስምምነት የተደመደሙ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ በ2002 ተደርጎ በነበረው የኑክሌር መሣሪያዎች ቅነሳ ፕሮግራም ላይ መፈራረም የቻሉበት ጉዳይ በስኬታማነቱ ይጠቀሳል።

ቀጣይ የሆነው የፕሬዚዳንት ፑቲን ውይይት ጆርጅ ቡሽን ተክተው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሆኑት ባራክ ኦባማ ጋር ነበር።
ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ወቅት በሁለት የምርጫ ጊዜያት ለስምንት ዓመታት ሩሲያን ከመሩ በኋላ ሥልጣናቸውን ለድሚትሪ ሜድቬዴቭ አስረክበው ሩሲያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እያገለገሉ ነበር።
ሩሲያን በፕሬዚዳንትነት ለአራት ዓመታት ያገለገሉት ድሚትሪ ሜድቬዴቭ ከአራት ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ ክሬምሊንን ለፑቲን አስረክበው ወጡ።
ፑቲን ከአራት ዓመታት በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር እያሉ አግኝተዋቸው ከነበሩት ባራክ ኦባማ ጋር ፕሬዚዳንት ሆነው ዳግም ተገናኙ።

በዚህም መሠረት በቡድን 8 እና ቡድን 20 ጉባኤዎች እንዲሁም በሁለትዮሽ ውይይቶች አና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በድምሩ ለዘጠኝ ጊዜያት ተወያይተዋል።
ሩሲያ እ.አ.አ 2013 ለቀድሞው የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ኤጀንሲ አባል እና ምሥጢራዊ መረጃዎችን አሾልኮው ከሀገር ለኮበለለው ኤድዋርድ ስኖውደን የፖለቲካ ጥገኝነት በመስጠቷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ቅሬታ ተፈጠረ።
በ2014 ደግሞ ሩሲያ ክሬሚያን አጠቃልላ በመያዟ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገሪቱ ላይ ማዕቀብ ጣሉ፤ በዚህ ወቅት የአሜሪካ እና የሩሲያ ግንኙነት ከቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በበለጠ ሁኔታ መቀዛቀዙ ይነገራል።
ቀጣዩ የፑቲን ውይይት በ2017 ላይ ከተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ነበር። ሁለቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ጀርመን ሀምቡርግ ላይ ተካሂዶ በነበረው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ ነበር።

በዚህ ወቅት ከጉባኤው ጎን ለጎን ተካሂዶ በነበረው የሁለትዮሽ ውይይት ላይ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የተገናኙት ፑቲን በመግባባት ላይ የተመሠረት የሚመስል እንደሆነ የተነገረለት ረጅም ውይይት አካሂደው ነበር።
በዚህ ውይይት ላይ ሁለቱ መሪዎች በዩኤስ-ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ሰሜን ኮሪያን በሚመለከቱ ጉዳዮች፣ በሶሪያ በነበረው ግጭት ዙሪያ እና በሌሎች ጉዳዮች መክረዋል።
ውይይቱ ለ35 ደቂቃዎች ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ለሁለት ሰዓታት ያህል ተራዘሞም ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በአጠቃላይ ለስድስት ጊዜያት ያህል ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ፑቲን በተለያዩ ጊዜያት ከአሜሪካ መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ትራምፕን ተክተው ወደሥልጣን ከመጡት ጆ ባይደን ጋርም የቀጠለ ቢሆንም ከሌሎች የአሜሪካ መሪዎች አንጻር ፑቲን እና ጆ ባይደን የተገናኙት በ2021 በጄኔቫ ተካሂዶ በነበረው የሳይበር ሴኪውሪቲ ጉባኤ ላይ ብቻ ነው።

በአጠቃላይ ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ ፕሬዚዳንት ሆነው በክሬምሊን በቆዩበት 25 ዓመታት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሉ ያደረጓቸውን ሁለት ውይይቶችን ጨምሮ ከቢል ክሊንተን ጋር ለ4 ጊዜያት፣ ከጆርጅ ደብሊው ቡሽ ጋር 28 ጊዜያት፣ ከባራክ ኦባማ ጋር 9 ጊዜያት፣ ከጆ ባይደን ጋር 1 ጊዜ እንዲሁም በዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የፕሬዚዳንትነት ወቅት ለ6 ጊዜያት በድምሩ 48 ጊዜያት ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ኋይት ሐውስ ከገቡ በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በአላስካ ይገናኛሉ። ይህም ፕሬዚዳንት ፑቲን ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ጋር ያደረጉት 49ኛው ውይይታቸው ይሆናል።
የአሁኑ የሁለቱ መሪዎች ውይይት በዋናነት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ላለው ጦርነት መፍትሔ እንደሚያመጣ የታሰበ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል። ለመረጃው አልጀዚራን እና አሶሼትድ ፕሬስን በምንጭነት ተጠቅመናል።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #Russia #USA #diplomacy #worldpolitics