በአፋር ክልል 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያለው የአውስትሮሎፒቲከስ ቅሪተ አካል መገኘቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ፡፡
በክልሉ የቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም እና ቅርስ ጥበቃ ዳይሬክተር መሃመድ ሀሰን፤ የአፋር ምድር ከዚህ ቀደም የተለያዩ ቅሪተ አካሎች የተገኙበት ስፍራ መሆኑን ገልፀው፤ በእነዚህ ግኝቶችም ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት ፍሰት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
አዲስ የተገኘው ቅሪተ አካል የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ለመሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።
በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ''ሌዲ ገራሩ'' በተባለ ስፍራ የተገኘው ቅሪት አካል ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ ግኝት መሆኑን አቶ መሃመድ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስትም ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ጋር በመሆን በክልሉ ትልቅ ሙዚየም ለመገንበት ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል።
የአፋር ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጥናት እና ምርምሮችን በማጠናከር የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በሁሴን መሀመድ