የጎቤ እና ሺኖዬ በዓል የኦሮሞን ህዝብ ባህላዊ ስርዓት በጠበቀ መልኩ መከበር አለበት ሲሉ የኦሮሚያ አባ ገዳዎች መልዕክት አስተላለፉ።
ኦሮሞ ከነሃሴ ወር መገባደጃ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ የዝናብ ወቅት ማለቁን፣ የፀደይ ጊዜ መምጣቱን፣ ከተፈጥሮ እና ወቅታዊ ዑደቶች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳይበት የተለያዩ በዓላትን የሚያከብርበት ጊዜ ነው።
ከነዚህ መካከል የሺኖዬ እና የጎቤ በዓልም ከጷግሜ መጨረሻ እስከ መስቀል ድረስ የሚከበር ሲሆን፤ እድሜያቸው ከአስራዎቹ መጀመሪያ እስከ ሃያዎቹ አጋማሽ ድረስ ያሉ የኦሮሞ ልጃገረዶችና እና ወጣት ወንዶች ተሰባስበው የሚያከብሩት ነው።
በበዓሉ ወቅት ወጣቶች ጥሩ መዓዛ ያለው ሣር በመያዝ ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በባህላዊ ውዝዋዜዎች፣ በዘፈኖች እና በጭፈራዎች መልዕክት የሚያስተላልፉበትና ምርቃት የሚቀበሉበት ነው።
በዓሉን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ አባገዳዎች፤ በዓሉ አንድነትን፣ ፍቅርና መከባበርን የሚያሳይና ነባር ባህላዊ እሴቶችን ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍበት እንደመሆኑ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዘሃራ መሀመድ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #ጎቤ #ሺኖዬ