ነገ በሚጀመረው ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ 4 ሺህ የሕብረተሰብ ክፍሎች አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ሁነት አስመልክቶ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ሮ መስፍን አርዓያ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ምክክሩ ተመካካሪዎች ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገውና ተመካክረው የሰላሙን መንገድ ያቀናሉ የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
አክለውም ነገ የሚጀምረው የሀገራዊ ምክክር መድረክ ታሪካዊውን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ ወደ መዲናዋ የገቡት ጉባኤተኞች በአምስት መቶ ተከፋፍለው ለ30 ቀናት በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት የሚወያዩ ሲሆን፣ በዚህ ሂደትም በሀገራችን ዋና ዋናና መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የታላቁን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መጀመር ዋዜማ አስመልክቶም፣ ከኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ጀምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ ስፍራዎች የመከላከያ ማርሽ ባንድ ደማቅ የሙዚቃ ትርዒት እያቀረበ ይገኛል።
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላምና አንድነት አዲስና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀው ይህ ታሪካዊ መድረክ፣ ሁሉም ተመካካሪ ሀገራዊ ኃላፊነቱን በሰከነና በበሰለ መንገድ እንዲወጣ ታላቅ አደራ የተጣለበት መሆኑም ተመላክቷል።
በቶማስ ኃይሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: