በአሁኑ ወቅት ዓለም በከፍተኛ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት፣ ባልተገመቱ ለውጦችና በውስብስብ ሽግግሮች ውስጥ እያለፈ ይገኛል።
ትናንት የነበሩ አስተማማኝ ትብብሮች ዛሬ ሲፈርሱ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተሰሚነት ሲሸረሸርና የኃይል ሚዛኑ ከአንድ ዋልታ ወደ ብዙ ዋልታዎች ሲዛወር እያስተዋልን ነው።
በዚህ እጅግ ተለዋዋጭና አሻሚ በሆነ ዓለም አቀፋዊ አውድ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊና ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የሚገኙ ሀገራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውን እንዴት መቅረጽ አለባቸው የሚለው ጥያቄ የህልውና ያህል ከባድ ነው።
በተለምዶ የውጭ ፖሊሲ በጽኑ ርዕዮተ-ዓለማዊ መርሆችና በረጅም ዘመን ወዳጅነቶች ላይ ይመሰረት ነበር። ሆኖም አሁን ያለው የዓለም ሁኔታ ይህንን ቀመር ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
አሁን የሚያዋጣው አካሄድ ርዕዮተ-ዓለማዊ መነጽርን አውልቆ በየእለቱ ለሚቀያየረው ዓለም አቀፋዊ እውነታ የሚመጥን ስልታዊና ተግባራዊ (Pragmatic) እርምጃዎችን መውሰድ ብቻ ነው።
ይህንኑ ነባራዊ ሀቅና የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ ያደረጉት ንግግር የሀገራችንን አዲስ የስትራቴጂ አስተሳሰብ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታና የኢትዮጵያን አቋም ሲያብራሩ እንዲህ ብለው ነበር “ኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ በሆነ አውድ ውስጥ የሚኖረን ፖሊሲ ፕራግማቲክ መሆን ካልቻለ በቋሚነት አንድ መርህ ማስቀመጥ ያስቸግራል፤ መስፈሪያው ብሄራዊ ጥቅም ሆኖ ገቢር ነበብ (ፕራግማቲክ) በሆነ መንገድ መሄድ ያስፈልጋል።
የሀገራችን መርህ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው። ሌሎች ከፍላጎታችን ፈቀቅ በሚያደርገን ልክ ተጽዕኖ እንዲያደርጉ አለመፍቀድ ነው።”ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ተግዳሮቶች የተማረችውን ትምህርት ወደ ስትራቴጂክ መመሪያ የለወጠችበት ማሳያ ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ ከባህላዊው “የነባር ወዳጆች ታማኝነት” ዲፕሎማሲ ወጥታ ወደ “ስትራቴጂካዊ ራስን መቻል” መሸጋገሯን እንረዳለን። በተለይም “ውሃ ሲደፈርስ አትቅዳ” የሚለው የሀገር በቀል እውቀት ፍልስፍና በጂኦፖለቲካው መድረክ ትልቅ ትርጉም አለው።
ዓለም አቀፍ ኃይሎች በየቀጣናው ግጭቶችንና ቀውሶችን በመፍጠር (ውኃውን በመድፈርስ) ትናንሽ ሀገራት ሳይወዱ በግድ ወደ አንዱ ወገን እንዲጠጉና ጥቅማቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ይጫኗቸዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ የደፈረሰ ውኃ ውስጥ በስሜት ከመግባት ይልቅ፣ የቆምክበትን መሬት አጽንተህ መታገስና ነገሮች ሲጠሩ የራስን ጥቅም ማስጠበቅ የሚለውን ብልሃት መምረጧን ያሳያል።
ይሄ የጥንቃቄና የብልሃት ስልት ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ማዕበል ውስጥ እንዳትሰምጥ የሚያደርግ የደህንነት ጋሻ ነው።
በዚህ አዲስ አቅጣጫ ውስጥ እጅግ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ሀገራችን ተግባራዊ እያደረገችው ነው የተባለው የ“ሦስቱ መ” (መቋቋም፣ መጠቀም፣ መግራት) መርህ ነው።
ይህ መርህ በባዕዳን አጀንዳ ላይ ተንጠልጥሎ ከመኖር የመውጫ ስትራቴጂ ነው።
የመጀመሪያው ‘መ’- መቋቋም- የሚጀምረው የውስጥ አቅምን ከመገንባት ነው።
ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ወረርሽኞች፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ የየመን ቀውስ፣ የአሜሪካ - እስራኤል እና ኢራን ጦርነት የዓለምን የንግድና የነዳጅ መስመር ሲያስተጓጉሉ፣ “አፍሪካ በረሃብ ልትአልቅ ነው” የሚል የሟርት መዝሙር በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በስፋት ተዘምሮ ነበር።
ሆኖም ኢትዮጵያ ይህንን የውጭ ጫና ለመቋቋም የውስጥ ግብርና አቅሟን ማሳደግና ስንዴን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት ላይ ማተኮሯ፣ ሟርቱን በተግባር የመስበር ስትራቴጂ ነበር።
ሁለተኛው ‘መ’- መጠቀም ሲሆን ፈተናዎችን ወደ ዕድል የመቀየር ጥበብ ነው። የዓለም ኃይሎች እርስ በርስ ሲጋጩ የሚፈጠሩትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ክፍተቶች አይቶ ለአገር ጥቅም ማዋልን ይጠይቃል።
ሦስተኛውና እጅግ የላቀው የስትራቴጂ ደረጃ ደግሞ ‘መግራት’ ነው። መግራት ማለት ሌሎች በጫኑብህ አጀንዳ ላይ ምላሽ ሰጪ (Reactive) መሆን ማቆም ሲሆን ይልቁንም የራስህን አጀንዳ ቀርጸህ ሌሎችን በአንተ የጨዋታ ሕግ ውስጥ እንዲጫወቱ ማድረግ (Proactive) ማለት ነው።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት ተጠቅማ የሕዳሴውን ግድብ ማጠናቀቋና የቀጣናዊ ትስስር አጀንዳዎችን ቀርጻ መንቀሳቀሷ የዚህ “የመግራት” አቅም ማደጉ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህ የኢትዮጵያ ገቢርነበብ (Pragmatic) የውጭ ፖሊሲና የስትራቴጂክ ገለልተኝነት ጉዞ ቀላል የሚባል አይደለም።
የውሳኔ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅና በቀላሉ ሸብረክ ላለማለት ዋጋ ያስከፍላል። ነገር ግን ሁለት ታላላቅ የዓለም ጦርነቶችን ታሪክና ውጤት በጥንቃቄ ከመረመረች ሀገር የሚጠበቀው ዋናው ቁምነገር፣ ከታሪክ መማርና የራስን ድክመት በጊዜ መሙላት ነው።
ኢትዮጵያ አሁን እየተከተለችው ያለው መንገድ፣ ካለፈው ታሪኳ ያገኘችውን ጽናት ከአሁኑ ዘመን የብልሃት ዲፕሎማሲ ጋር በማዋሃድ፣ በደፈረሰው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ የራሷን የነፃነት ስልጣኔ የምታጸናበት አዲስ ምዕራፍ ነው።
ይህ አካሄድ ሀገራችንን ከአደጋ ከመጠበቁም በላይ በዓለም መድረክ ላይ ተገዢ ሳይሆን የራሷን ዕድል በራሷ የምትወስን ባለታሪክ አገር አድርጎ ያቆያታል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: