በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ተጠባቂ በሆነው የመጀመሪያው የግማሽ ፍፃሜ መርኃ ግብር፣ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት በዳላስ ስታዲየም የአውሮፓ ሻምፒዮኗ ስፔን ከዓለም ዋንጫው ስኬታማ ቡድን ፈረንሳይ ጋር ለፍፃሜ ለማለፍ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የዚህ ጨዋታ አሸናፊ እሁድ በሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ከአርጀንቲና ወይም ከእንግሊዝ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፤ በአሰልጣኝ ዲዲዬ ዴሻው የምትመራው ፈረንሳይ በተከታታይ ለሦስተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ላይ በመድረስ አስደናቂ ጉዞ እያደረገች ትገኛለች።
በውድድሩ እስካሁን 16 ግቦች ያስቆጠረችው ፈረንሳይ በሩብ ፍፃሜው ሞሮኮን 2 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ፤ ምባፔ የገጠመው የቁርጭምጭሚት ህመም ስጋት ቢፈጥርም፣ በልምምድ ሜዳ በጥሩ ሁኔታ ላይ መታየቱ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ኪሊያን ምባፔ 20 የዓለም ዋንጫ ግቦችን በማስቆጠር የሊዮኔል ሜሲን የ21 ግብ ክብረ ወሰን ለመጋራት አንድ ግብ ብቻ ይቀረዋል።
በአንጻሩ የአውሮፓ ሻምፒዮኗ ስፔን ካለፉት 36 ጨዋታዎች ጀምሮ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሽንፈት ያልገጠማት ሲሆን አሰልጣኝ ሉዊስ ዴ ላ ፎንቴ ላሚን ያማልን እና ሮድሪን በመያዝ ፈረንሳይን ለመፈተን ተዘጋጅተዋል።
ላሚን ያማል እስካሁን ፈረንሳይን በገጠመባቸው ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን የማስቆጠር ታሪክ አለው። እንደ ሚኬል ሜሪኖ ያሉ ተቀያሪ ተጫዋቾችም ጨዋታ የመለወጥ ልዩ አቅም እንዳላቸው በተደጋጋሚ ታይቷል።
ስፔን በውድድሩ እስካሁን አንድ ግብ ብቻ ተቆጥሮባት፣ በተጋጣሚዎቿ መረብ ላይ11 ግቦችን ማስቆጠሯ የቡድኑን ሚዛናዊነት የሚያሳይ እንደሆነ እየተነሳ ይገኛል።
ሁለቱ ሀገራት በቅርብ ዓመታት ባደረጓቸው 10 ጨዋታዎች ስፔን የ7 ጊዜ የበላይነት አላት፤ በተለይም በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 1 አሸንፋ ማለፏ የሚታወስ ሲሆን፣ የዛሬው ጨዋታ ፈረንሳይ ምላሽ የምትሰጥበት ወሳኝ አጋጣሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በዘረንቶስ ሰለሞን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: