Search

ኢትዮጵያውያን መመካከር አይችሉም የሚለው ትርክት ተሰበረ!!

ማክሰኞ ሐምሌ 07, 2018 48

ለዘመናት በጥርጣሬ መነጽር፣ በሀሰት ትርክት  ሲታይ የነበረው፣ በብዙኃን ዘንድ እንደማይቻል ሲነገር የኖረው ሀቅ ዛሬ ላይ ሊቀለበስ፣ የውሸት ትርክትም ሊሰበር ነው።

"ኢትዮጵያ ትመክራለች፣ የራሷን ዕጣ ፈንታም ራሷ ትወስናለች!" ይህ ሀቅ  ለብዙዎች የማይዋጥ፣ ለተወሰኑት ደግሞ የማይታሰብ ህልም መስሎ ቆይቷል። ኢትዮጵያ በራሷ ጉዳይ መነጋገር፣ መመካከር፣ እንዲሁም የተበታተኑ ልጆቿን በአንድ የሰላም ጠረጴዛ ዙሪያ መሰብሰብ አትችልም ሲባል ለዓመታት ተሰምቷል።

የችግሮቿ ቋጠሮ ፈፅሞ የማይፈታ፣ የልዩነቶቿም ግድግዳ የማይናድ ተደርጎ ተስሏል። ነገር ግን፣ ይህንን አፍራሽ ትርክት በህሊና ሚዛን ስንመዝነው፣ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ይነሳል፦ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የዓለም ህዝቦች ያነሱ፣ ማሰብና መመካከር የተሳናቸው ፍጡራን ሆነው ነውን?

መልሱ፣ ፈፅሞ አይደለም! የዚህ የጥፋት ትርክት ምንጭ ከእኛ ችሎታ ወይም ማንነት ሳይሆን፣ ከውጭ ጠላቶቻችን እና ከሴራ ቋታቸው የሚመነጭ መርዝ ነው። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ይህች ታላቅ ሀገር እና ህዝቦቿ አንድነታቸውን ሲያጡ፣ ሳይደማመጡ እና እርስ በርስ ሲናቆሩ ለእነሱ ትልቅ የድል በዓል ነው።

ምክንያቱም፣ በወንድማማቾች የእርስ በርስ መከፋፈል እና ግጭት ውስጥ የራሳቸውን የጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥቅም በሰፊው ያስጠብቃሉ።

በርስ በርስ ጦርነትና አለመረጋጋት እቶን ውስጥ፣ የራሳቸውን ህልውና ለማስቀጠል እና የቀኝ ግዛት የወረራ ፍላጎታቸውን በተዘዋዋሪ ለማስፈጸም ይሯሯጣሉ። የኛ ልዩነት፣ መጠፋፋት እና መቃቃር፣ ለዘመናት ኢትዮጵያን ለማዳከም ለሚጥሩ የውጭ ጠላቶች፣ ለቀኝ ገዢ ኃይሎች እና ለወራሪዎች የተመቻቸ ፖለቲካዊ ሰርገኛ ጤፍ ነው።

እውነታው ግን ከዚህ ፍፁም የተለየ ነው። መነጋገር፣ መደማመጥ እና መመካከር ለኢትዮጵያውያን ከማንም በላይ የተሻለ የፈውስ እና የዕድገት ዕድል ነው።

ኢትዮጵያውያን መነጋገር ከማንም በላይ ይችላሉ! ይህች ሀገር የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ብቻ ሳትሆን፣ ከጥንት ጀምሮ የተወሳሰቡ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ የዳበሩ ባህሎች እና አገር በቀል የስነ-ምግባር እሴቶችን የገነባች ማህፀን ናት። በገዳ፣ በጆካ፣ በሶንጎ፣ በማዳዓ እና በሌሎችም በርካታ የሽምግልና ሥርዓቶቿ፣ ጠብን በዕርቅ፣ ጦርነትን በሰላም፣ ልዩነትን በመግባባት የመፍታት ጥልቅ ማህበራዊ ካፒታል አላት።

ኢትዮጵያውያን በባህላቸው፣ በስነ-ቃላቸው እና በአኗኗራቸው የውይይትን እና የመመካከርን ስልጣኔ በተግባር ያዳበሩ፣ በዋርካ ስር ተቀምጠው ሸለቆ የሚያህል ችግርን በምላስ እና በልብ ልዕልና የሚደፍኑ ጥበበኛ ህዝቦች ናቸው።

ታዲያ ይህ ሁሉ ፀጋ እያለን፣ ለምን የውይይት ድርቅ መታን ብለን ስንጠይቅ፣ ጠላቶቻችን የዘሩብን የመጠራጠር አረም እና የፖለቲካ ስብራታችን የፈጠረው ጥላቻ መሆኑን እንረዳለን።

ዛሬ ግን ይህ የጠላት ሴራ ያበቃለታል። ያ የጨለማ ትርክት፣ "ኢትዮጵያ አትችልም፣ አትመክርም፣ አትስማማም" የሚለው የባዕዳን ምኞት ነገ፣ በይፋ ሐምሌ ስምንት ቀን 2018 ዓ.ም ከስረ-መሰረቱ ይናዳል!

ዓለም አይኑን አፍጦ እያየ፣ የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ ታላቅ አዳራሽ ተሰብስበው፣ የጠመንጃን አፈሙዝ ዘግተው በጠረጴዛ ዙሪያ የሀሳብ ሙግት ይጀምራሉ። የልዩነት እና የጥላቻ ግድግዳ ፈርሶ፣ የህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና የመግባባት ዴሞክራሲ ማለዳ ይበሰራል።

"ኢትዮጵያውያን አይችሉም" የሚለው የታሪክ ቅጥፈት ተሰብሮ፣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ትወጣለች። ያልተካሄደበትን የምክክር መንገድ በመጓዝ፣ የሀሳብ ልዕልና የጦር መሳሪያን ድምፅ ዝም ያሰኘዋል።

የራሳችንን አጀንዳ በራሳችን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠን ስንመክር፣ ሉዓላዊነታችን በተግባር ይረጋገጣል የጠላት አንገትም ይደፋል።

አዎ፣ ኢትዮጵያ ትመክራለች! ኢትዮጵያ ትወስናለች! በልጆቿ የጠረጴዛ ዙሪያ ስምምነት፣ የዘመናት ጠላቶቿን አሳፍራ፣ በአንድነት እና በክብር ለዘላለም ፀንታ ትኖራለች! ይህ ታላቅ የምክክር ጉባኤ፣ የውድቀታችን ማሳረጊያ፣ የትንሳኤያችን ደማቅ ብስራት ነው!!

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: