የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፣ ለታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች በሙሉ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ታላቅ አደራና ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ መልዕክት አስተላለፉ።
ዋና ኮሚሽነሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ታሪካዊ በሆነው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ የመጣችሁትን ወገኖቼን ለመቀበል በመታደሌ ታላቅ ክብር ይሰማኛል" ብለዋል፡፡
እያንዳንዱ ተመካካሪ ለጉባኤው ሲመጣ የወከለውን ማኅበረሰብ ድምፅና ትክክለኛ ምኞት ለማስተጋባት ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገራችን የጋራ ዕድልና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ፅኑ መሠረት ለመጣል ጭምር በመሆኑ በትከሻቸው ላይ የወደቀው ብሔራዊ ኃላፊነት እጅግ ታላቅና ጥልቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ አያይዘውም፤ ተመካካሪዎች በሂደቱ በሚያደርጉት ምክክርና ውይይት የሚደርሱባቸው ውሳኔዎች፣ የሚፈጥሩት ብሔራዊ መግባባት እንዲሁም የሚያጸኑት ዘላቂ ስምምነት ከዚህ የታሪክ ወቅት ባለፈ እጅግ ዘልቆ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ለሰላማዊት፣ ለዴሞክራሲያዊትና ለተግባባች ኢትዮጵያ ዘላቂ መሠረት የሚጥል ታሪካዊ ክንውን መሆኑን በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፣ የታላቁ ጉባኤ ተመካካሪዎች የሚያደርጉት እያንዳንዱ ምክክር በጥበብ፣ በጋራ መከባበርና ለሕዝብ ጥቅም ባላቸው ጽኑ ቁርጠኝነት እንዲመራ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ብሩህ ነገን የሚያሰናዳ ታሪካዊ ስኬት እንዲሆንላቸው ያላቸውን ልባዊ ምኞት ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: