ጀግንነት ሲነሳ ሁልጊዜም ወደ አዕምሯችን ቀድሞ የሚመጣው የጦር ሜዳ ውሎ፣ የጠመንጃ ድምፅ እና የጡንቻ ጉልበት ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን፣ እውነተኛ ጀግና ማለት ከራሱ በላይ ለሀገሩ ክብር ሲል የሚቆም፣ ለህዝቡ ዘላቂ ጥቅም ሲል ከግል ስሜቱ ዝቅ የሚል የሚወርድ ማለት ነው። ጀግና ማለት በሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም ፊት ሁሌም በፅናት የሚቆም፣ ሀገሬ ትፅና እንጂ የእኔ የግል ጥቅም ጉዳዬ አይደለም ብሎ የግል ጥቅሙን የማያስቀድም ታላቅ ሰው ነው።
የጀግንነት የመጨረሻው ጥግ፣ የራስን ስሜት እና ፍላጎት ገድቦ ለጋራ ማህበራዊ ስምምነት ራስን ሙሉ በሙሉ ማስገዛት ነው።
እነሆ ከነገ ጀምሮ በእናት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ታሪካዊው አገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ የነዚህ እውነተኛ ጀግኖች መሰብሰቢያ ስፍራ ይሆናል።
በምክክሩ ስፍራ የሚገኙት ተሳታፊዎች በሙሉ በተግባር ጀግኖች ናቸው። ለምን ቢባል፣ ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያውያን በመመካከር እና በመደማመጥ ያሸንፋሉ ብለው በፅኑ ስላመኑ ነው።
እነዚህ የሰላም አርበኞች የምክክሩን አንገብጋቢ አስፈላጊነት በጥልቀት ተረድተዋል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በምክክር ጠረጴዛ ዙሪያ ሰጥቶ መቀበል የሚባል የሰለጠነ መርህ መኖር እንዳለበት በልባቸው ተቀብለዋል። ጀግኖች ጥቅማቸውን በማጣጣም ለሀገራቸው ሲሉ የጋራ መፍትሄ ያመጣሉ።
በተቃራኒው ደግሞ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ነው መሆን አለበት የሚል ግትር፣ እንዲሁም እኔ ብቻ ነኝ ልደመጥ የሚገባኝ የሚል ራስ ወዳድ ሰው ፈፅሞ ወደ ምክክር መድረክ አይገባም።
እንዲህ አይነቱ ሰው የሀሳብ ሙግትን ስለሚፈራ፣ የምክንያት ልዕልና ስለሚያስጨንቀው ምክክሩን ሸሽቶ ይሄዳል።
የሌላውን ሀሳብ ለማዳመጥ ትዕግስት የሌለው አካል፣ የጀግንነት ልብ የለውም። ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን፣ የተለየ ሀሳብ ካለው ወንድም ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ፣ በመከባበር መነጋገር መቻልን ይጠይቃል።
እልህን አሸንፎ፣ ትዕቢትን ጥሎ፣ ለሀገር ህልውና ሲባል መደራደር የጀግኖች ሁሉ ጀግንነት ነው። የግል ጥቅማቸውን በመተው፣ የህዝብንና የሀገርን የረዥም ጊዜ ብሩህ ተስፋ እውን ለማድረግ ሲሉ ጀግኖች ዘወትር ከፊት መስመር ይሰለፋሉ።
ምክክር የፈሪዎች መሸሸጊያ ሳይሆን፣ እውነተኛ የሀገር አርበኞች ፍርሃትን፣ ጥርጣሬን እና ጥላቻን ረግጠው የሚያልፉበት የድል አውድማ ነው።
ለሀገር ክብር ሲባል ራስን ዝቅ ማድረግ ከምንም በላይ ታላቅ አሸናፊነት መሆኑን በተግባር ያረጋግጣሉ። ስለሆነም፣ የጀግና ትክክለኛ መገኛው ምክክር ነው! ጀግና ቦታው የውይይት አውድማ፣ የሀሳብ ፍጭት እና የዕርቅ ጠረጴዛ ነው።
ሀገር የምትድነው፣ የምትፀናው እና ወደፊት የምትሻገረው፣ እነዚህ ጀግኖች የራሳቸውን ጥቅም አጣጥመው እና አቻችለው ለታላቂቱ ኢትዮጵያ ሲሉ በአንድነት ሲቆሙ ብቻ ነው።
ነገ ሐምሌ 8፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አዲስ ታሪክ ሊሰሩ በአንድነት ይመከራሉ። የሰላም፣ የይቅርታ እና የመግባባት ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ ከጠመንጃ አፈሙዝ ይልቅ ጠረጴዛን የትግል አውድማቸው ያደረጉ ጀግኖች ሀገራችንን ከችግር አዙሪት አውጥተው ወደ ብርሃን ያሻግሯታል።
አዎ፣ የጀግና መገኛው ምክክር ነው፤ ኢትዮጵያም በጀግኖች ልጆቿ የምክክር ጥበብ እና መደማመጥ ለዘላለም አሸናፊ ሆና በክብር ወደ ፊት ትዘልቃለች! ይህ ታሪካዊ ሂደት ለትውልድ የሚተላለፍ እውነተኛ የድል አሻራ ሆኖ በደማቁ ይፃፋል፤ ምክንያቱም እውነተኛ ጀግንነት መገኛው ጦርነት ሳይሆን ሰላም ነው።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: