ሁለቱ የዓለም ኃያላን ሀገራት መሪዎች ከ3 ዓመት በላይ የዘለቀውን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትላንት ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት ተጠናቋል፡፡
የአሜሪከው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው አቻቸው ቪላድሚር ፑቲን ትላንት ምሽት በአሜሪካ በስተሰሜን ምእራብ በአላስካ ግዛት 3 ሰዓታትን የፈጀ ውይይት ካደረጉ በኋላ ለ12 ደቂቃዎች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
መሪዎቹ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል የተቁስ አቁም ስምምነት ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመግለጫቸው ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር እጅግ በጣም ፍሬያማ ውይይት አድርገናል፤ በብዙ ነጥቦችም መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን የቀሩ ጥቂት ጉዳዮች ቢኖሩም፤ በበርካታ በግልፅ ባልተነገሩ ጉዳዮች ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫው አስታውቀዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ግን ወደፊት ከዩክሬን እና ኔቶ ጋር ሊሰሩ የሚገባቸው ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፤ በሁለቱ ሀገራቱ መካከል በመከባበር መንፈስ የተሞላ እግጅ ጠቃሚ ድርድር መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ ይህ ድርድር እንዲካሄድ ሁኔታዎችን በማመቻቸቷም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
"በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ያለው አለመግባባት በድርድር እንዲቋጭ ለብዙ ጊዜያት በስልክ በግልፅ ተነጋግረናል፤ ተወካዮችን ልከን ተወያይተናል፤ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ትራምፕ አስፋላጊውን ሁኔታ እያመቻቹ ነው፤ የዩክሬን ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የሩሲያ ብሄራዊ ደህንነት ባከበረ መንገድ መሆን አለበት፤ ለዚህም ቁርጠኞች ነን" ብለዋል የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን፡፡
በላሉ ኢታላ
#EBC #ebcdotstream #russia #usa