አንድ ሰው በህንፃ ላይ ያለ መስታወት አንፀባርቆበት አይኑ ላይ ጉዳት ቢደርስ እና በህክምና ቢረጋገጥ የህንፃው ባለቤት ተጠያቂ የሚሆንበት አግባብ አለ ወይ ሲል ህጉ ምን ይላል የቅዳሜ መልክ ፕሮግራም ጠይቋል፡፡
የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አቤል ዘውዱ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኃላፊነትን በትክክል ባለመወጣት የሚፈጠር ድንገተኛ አደጋ በህግ ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለፃ ክስ ከመመስረቱ በፊት በመጀመሪያ ጉዳት መድረሱ በህክምና መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
በህክምና መረጋገጥ የማይችል ከሆነ በሌሎች ደጋፊ ማስረጃዎች መረጋገጥ መቻል እንደሚኖርበት ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
የህንፃው ባለቤት መስታወቱን በሚገጥምበት ወቅት ከደረጃ በተቻ የሆነ መስታወት ገጥሞ ከሆነ ሰው ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መስታወት በመግጠሙ ምክንያት ጥፋተኛ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላልም ነው ያሉት፡፡
በህንፃው ግንባታ ወቅት የተሳተፉ ባለሙያዎች፣ ኮንትራክተሩ ወይም አማካሪው ጋር የነበረ ጥፋት ከሆነ ደግሞ እነሱ ሊጠየቁ የሚችሉበት የህግ አግባብ መኖሩን ገልፀዋል፡፡
ጉዳቱ ከተረጋገጠ በኋላ ተጎጂው ከዚህ ቀደም ከነበረው የመስራት አቅሙን ምን ያህል ቀንሶታል የሚለው ጥያቄ ይነሳል ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ይህም በህክምና ባለሙያ ተረጋግጦ የጉዳቱ መጠን እና ተጎጂው የሚያገኘው ገቢ ተሰርቶ ለፍድ ቤት ከማስረጃ ጋር ተደግፎ በማቅረብ ክስ መመስረት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ባሸገር አንዳንዴ ጥፋተኛ የሆነ አካል የማይኖርባቸው አጋጣሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አንስተዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#ebc #ebcdotstream #የቅዳሜመልክ