የአፍሪካ ሕብረት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የሚመራና የኢትዮጵያውያን በሆነው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ ጽኑ እምነት እንዳለውና እንደሚደግፍ የሕብረቱ የፖለቲካ፣ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ሀገራዊ ምክክር “ታሪካዊ” ሲሉ ያወደሱት ኮሚሽነሩ፣ ሕብረቱ የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል በመሆኑ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።
ለምክክሩ ስኬታማነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና የልማት አጋሮች እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎም አድንቀዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን፣ ለውጥንና ዕድገትን ለማምጣት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ምክክር የሀገራዊ ኃላፊነት መገለጫ እንዲሁም ሰላማዊ መፍትሄዎችን ለማምጣት ዋስትና ነው ያሉት አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፣ ሀገራዊ ባለቤትነት ያላቸው ሰላማዊ መፍትሄዎች ለሁለንተናዊ እድገት መሠረት ናቸው ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋትና አንድነት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እንዲሁም ለመላው አሕጉር የሚተርፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አሁንም ቢሆን ሰላምን ለማስረጽ፣ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ዘላቂ ልማትን ለማምጣት እንዲሁም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ህልም እንዲሳካ ከጎናችሁ ይቆማል፤ ይህ ጉዞ የአፍሪካን የብልጽግና ጉዞ ከሚወስነው “አጀንዳ 2063” ጋር እጅግ የተጣጣመ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን በጋራ መግባባት እና መተማመን ላይ የተመሰረቱ ውይይቶችን እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።
የምክክር ጉባኤው መርሆዎች የዴሞክራሲ እሴቶችን እና አካታችነትን በጽኑ የያዙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ሕብረቱ ለሂደቱ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: