ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ያደረጉት ጥልቅ ንግግር፣ ለኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለውን ፋይዳ በሚገባ ያመላከተ ታሪካዊ ንግግር ነው።
የንግግሩ ዋና ዋና ሐሳቦች በሀገራችን የፖለቲካ ባህል ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት እና ሀገራዊ ምክክሩ ይህንን እውን ለማድረግ ያለውን ወሳኝ ሚና አሳይተዋል።
የኃይል አዙሪትን በመስበር ተቋማዊ የፖለቲካ ባህልን መገንባት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ "በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይል እርምጃ የሚደመደም" መሆኑ በንግግሩ በግልጽ ተነሥቷል።
ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የዚህ ሐሳብ ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው። አንዲት ዘመናዊ ሀገር ልትገነባ የምትችለው የፖለቲካ ልዩነቶች በጦር መሣሪያ ሳይሆን በሐሳብ ልዕልና ሲዳኙ ብቻ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ ይህንን የዘመናት የታሪክ ስብራት በማከም፣ ግጭትን ወደ ዴሞክራሲያዊ የውይይት መድረክ የሚያሸጋግርበትን ምኅዳር ይፈጥራል።
ይህ ማለት ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወጥተን ሐሳብን በነጻነት ወደ መግለጽና ተቋማዊ አሠራርን ወደ ማዳበር እንሸጋገራለን ማለት ነው፤ ይህም ለዘላቂ ሰላም እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና አለው።
የውስጥ አንድነትን በማጽናት ሉዓላዊነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነትን መከላከል ቁልፍ ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከብት ሲገዛ የሌሉ አሞራዎች ሲታረድ ግን ያንዣብባሉ" በማለት ያቀረቡት ዘይቤ፣ የውስጥ መከፋፈል ለውጭ ኃይሎች መፈንጫነት እንዴት እንደሚያጋልጥ በጥልቅ ያሳያል።
የምክክሩ ፋይዳ ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በውይይት ፈትተው ጠንካራ የውስጥ አንድነት እንዲፈጥሩ ማስቻል ነው። ይህ ሲሆን የውጭ ኃይሎች በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በሩን ይዘጋል።
ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር መቻል፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደራዳሪነት ከፍ የሚያደርግ እና የሀገርን ሉዓላዊነት በማያወላውል ሁኔታ የሚያስከብር ነው።
አቃፊነት እና እኩልነትን በማረጋገጥ የብዝኃነት አስተዳደርን ማጎልበት በዘመናዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የብዝኃነት አስተዳደር መሠረታዊ ምሰሶ ነው።
ሕዝቦች አንዱ ሌላውን ማዳመጥ እንዳለባቸው የተሰጠው አቅጣጫ ለሀገር ግንባታው ያለውን ፋይዳ ያጎላል። እውነተኛ እና ጽኑ ሀገር የምትገነባው የሁሉም ዜጎች ድምፅ እኩል ሲሰማ እና ማንም ከመድረኩ ሳይገፋ ማካተት ሲቻል ነው።
ይህ አካታችነት ብሔራዊ መግባባትን ያጠናክራል፣ የዜጎችን ሀገራዊ የባለቤትነት ስሜት ከፍ ያደርጋል፣ እንዲሁም በሕዳግ ላይ ያሉ ማኅበረሰቦችን ወደ ማዕከላዊ የፖለቲካ ተሳትፎ በማምጣት ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ያመጣል።
ሀገር በቀል እሴቶችን ለዘመናዊ መንግሥት ግንባታ መሠረት ማድረግ የ"ዋርካ" ተምሳሌት እና የሽምግልና ባህል በንግግሩ መነሣታቸው፣ የኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ ከውጭ በሚመጡ ንድፈ ሐሳቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በራሷ ሀገር በቀል እሴቶች ላይ መቆም እንዳለበት ያሳያል።
የምክክሩ ትልቁ ፋይዳ ሕዝቡ የሚያውቀውን እና የሚያከብረውን የእርቅ፣ የይቅርታ እና የመደማመጥ ባህል ወደ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ማምጣት ነው። ይህ አካሄድ ሕዝቡ በሒደቱ ላይ እምነት እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር፣ ከኢትዮጵያውያን ሥነ-ልቦና ጋር የተዋሐደ እና ሥር የሰደደ ዘላቂ የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ለመፍጠር ያስችላል።
የሰላማዊ ሥልጣን ሽግግር ባህልን እና ሕገ መንግሥታዊ ጽናትን ማረጋገጥ አራት ሺሕ ሰዎች ተሰብስበው የሚመክሩበት ይህ መድረክ፣ በቀጣይ ለሚኖረው አዲስ ሥርዓት እና ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ጠንካራ መሠረት ይጥላል።
የዚህ ውይይት ለሀገር ግንባታ ያለው የላቀ ፋይዳ፣ በጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ፈቃድ ላይ የተመሠረተውን የቀድሞ አሠራር በመቀየር እጅግ ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ ያለበት ማኅበራዊ ውል መፍጠሩ ላይ ነው። ይህ ከታች ወደ ላይ የተገነባ ሰፊ የጋራ መግባባት በቀላሉ የማይፈርስ ተቋማዊ መዋቅር እንዲገነባ ያደርጋል። በተጨማሪም፣ ፖለቲካዊ ሽግግሮች ከግጭት ነፃ ሆነው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወኑ የማይናወጥ መሠረት ያስቀምጣል።
በአጠቃላይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቶች ሀገራዊ ምክክሩ፣ ዘመናዊት፣ አቃፊ እና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል የረጅም ጊዜ ማኅበራዊ ውል መሆኑን ያረጋግጣሉ።
ይህ አጋጣሚ ታሪካዊ ስህተቶችን አርሞ፣ ለነገው ትውልድ ጠንካራ እና የበለጸገች ሀገርን ለማቆየት የሚደረግ ታላቅ እና የተቀናጀ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እርምጃ ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: