Search

ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ፡ ሀገርን የሚታደግ አዲስ ታሪክ የመጻፍ ብርቅዬ ዕድል

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 71

ዛሬ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ አጋጣሚ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ያለፈ የታሪክ ስብራት፣ የአሁኑን ተጨባጭ ሁኔታ እና የወደፊቱን የትውልድ ዕጣ ፈንታ በጥልቀት አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግራቸውን የጀመሩት ይህ መድረክ ልባም ለሆኑ ሰዎች «ከታሪክ ብዕርና ብራና ፊት መቆም» ብቻ ሳይሆን ሀገርን የሚታደግ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችል ብርቅዬ ዕድል መሆኑን በመግለጽ ነው።

ይህ አባባላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሄደችበትን መንገድ ክብደት እና ተመካካሪዎቹ የተሸከሙትን ታሪካዊ ኃላፊነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።

የሼክስፒርን "በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ማዕበል አለ፤ ያንን ማዕበል ተጠቅሞ ከጎርፍ መውጣት ይቻላል" የሚለውንና የሰንዙን "ዕድሎች የሚበዙት በሚጠቀምባቸው ሰው ልክ ነው" የሚሉትን ሀሳቦች ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መነሻ ባደረጉት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ካሳለፈቻቸው መከራዎች በስተጀርባ ያሉትን ፈተናዎች ወደ ዘላቂ መፍትሔና ብልጽግና ለመቀየር የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ምክክር ዋነኛ አስፈላጊነት የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ሕመም ማከም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፋት አንስተዋል።

ሀገራችን ረጅም ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሀገር ብትሆንም በፖለቲካ ባህሏ ውስጥ ትልቅ ስብራት መኖሩንና ይህም "በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይል እርምጃ መደምደም" መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ስብራት ለማስረዳትም ከኢፋት እስከ ግቤ፣ ከወላይታ እስከ ከፋ፣ ከወሎ እስከ ሸዋ፣ ከላስታ እስከ ትግራይ የነበሩትን የታሪክ ሥርወ-መንግሥታት እንደ ማሳያ በመጥቀስ፣ በሁሉም ዘመን የታየው ውድቀት የኃይል እርምጃን የታሪካችን አካል ከማድረግ የመነጨ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህ ምክክር የተዘጋጀውም ይህንን በኃይል የመደማደም ፖለቲካዊ አባዜ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመግታት እና በውይይት የመፍትሔ አካል ለመሆን ነው።

የሀገራችን የውስጥ ደካማ ጎኖች ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በር እንደሚከፍቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲያስገነዝቡ የጠንባሮ አባቶችን "ከብት ሲገዛ የሌሉ አሞሮች፣ ከብት ሲታረድ በአካባቢው ያንዣብባሉ" የሚለውን ተረት አጣቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በውስጥ ስትናቆር እና ስትዳከም አድፍጠው የሚጠብቁና በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያደናቅፉ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንድታጣ እና የጂኦግራፊ እስረኛ እንድትሆን ያደረጋት ዋነኛው ምክንያት የውጭ ኃይሎች ጥንካሬ ሳይሆን በውስጥ በነበረን ስንፍናና ሴራ ነው።

አሁንም ቢሆን የውስጥ ልዩነቶች ወደ ግጭት ሲያመሩ እነዚህ "አሞሮች" ጥይት እና ፕሮፓጋንዳ ለማቀበል እንደሚፈጥኑ ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለሚያንዣብቡ ኃይሎች የቅርጫውን ባለቤት የሚወስነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑንና ከፈቃዱ ውጭ አንዲት ኪሎ ሥጋ እንኳን መውሰድ እንደማይቻል አስጠንቅቀዋል።

በቁጥር የበዙት በቁጥር አነስተኛ ለሆኑ ማኅበረሰቦች ዕውቅ እና መስጠትና ድምፃቸውን መስማት ለሀገር መጽናት ያለው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

እንደ ኦሮሞ እና አማራ ያሉ በቁጥር ትላልቅ የሆኑ ሕዝቦች እንደ ጋሞ፣ አሌ፣ ኮንሶ፣ ጎፋ እና ዳሰነች ያሉትን ማኅበረሰቦች ጥያቄ ካላደመጡና ካላከበሩ ኢትዮጵያን ማጽናት እንደማይቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም የሀገራችን አንድነት ሊጠበቅ የሚችለው በቁጥር ብልጫ ላይ የተመሠረተ ፍላጎትን በመጫን ሳይሆን እያንዳንዱ ወገን የሌላውን ጉዳት እያሰበ "ለኔ ሳይሆን ለእኛ፣ ለሰፈሬ ሳይሆን ለኢትዮጵያ" በሚል መርህ መንቀሳቀስ ሲችል ብቻ መሆኑን አስምረውበታ።

የኢትዮጵያን አብሮነትና ጽናት ከሀገርበቀል እውቀቶችና ከባህላዊ እሴቶች ጋር በማገናኘት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዋርካ" ለምክክር፣ ለሽምግልና እና ለዕረፍት የሚሆን ታላቅ ተምሳሌት አድርገው አቅርበውታል።

ባለፉት ዓመታት ዋርካን የመቁረጥ (የመወያየት ባህልን የማጥፋት) ዝንባሌ በመስፋፋቱ፣ "እኔ ብቻ ካልኩኝ" የሚል አደገኛ ልምምድ መተካቱን ገልጸዋል።

ይህንን ለማስተካከልም በትግራይ አባባሎች ውስጥ ያለውን "የአንድ ሰው ምክር ከምድር በታች ነው፣ የሁለት ሰው ከምድር በላይ ነው፣ የሦስት ሰው ምክር ግን ምርጥ ዘር ነው" የሚለውን ፍልስፍና ተጠቅመዋል።

አሜሪካኖች 55 ሰዎች ተወክለው የመቶ ዓመታት ሕገ-መንግሥት ሲገነቡ ኢትዮጵያ ግን ሁሉን ወገን ለማካተት 4 ሺህ ሰዎችን የሰበሰበችው የተሻለ ዘላቂና በቀላሉ የማይናወጥ ዘላቂ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ቀፎዋን የጣለች ንብ ማር አትሰጥም" በሚለው ምሳሌያዊ አገላለጻቸው ተመካካሪዎች ልባቸውን እና አእምሯቸውን በምክክር አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ እና ከምክክሩ አውድ ውጭ በሆኑ መልእክቶች የሚመሩ ከሆነ ምክክሩ ፍሬ እንደማያፈራ በመጠቆም፣ የውይይቱ ብርሃን ከመላው ኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካም ምሳሌ የሚሆን ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት ገልጸዋል።

በመሆኑም ተመካካሪዎቹ ለዛሬ ሳይሆን ለነገ፣ ለራሳቸው ሳይሆን ለልጆቻቸው በማሰብ የጀመሩትን ምክክር ወደ ውጤት እንዲቀይሩ የተጣለባቸው አደራ የኢትዮጵያን ቀጣይ ህልውና የሚወስን ታሪካዊ ክስተት ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: