ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍትበት፣ የቆዩ የፖለቲካና የማኅበራዊ ቁርሾዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ለመፍታት ያለመው ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በአጀንዳ ማሰባሰብና በተሳታፊዎች ልየታ ላይ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ አሁን ላይ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን በመለየት ከሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የተወከሉ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎችን በአንድ መድረክ አሰባስቧል።
የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከዚህ ቀደም ለጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት ማብራሪያ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዓድዋን መንፈስ በመሰነቅ ለሀገር ግንባታ ያዳበረውን ተግባር ወደ ምክክርና መግባባት መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል።
እንዲሁም በምክክሩ የሚተላለፉ ውሳኔዎችና የሚደረሱት ስምምነቶች ከዚህ የታሪክ ወቅት ባለፈ ዘልቀው የሚቀጥሉና ለሰላማዊ፣ ለዴሞክራሲያዊ እና መግባባት ለሰፈነባት ኢትዮጵያ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውንም ማመልከታቸው ይታወሳል።
ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን ለኢትዮጵያውያን አዲስ ተስፋ የሰነቀ፣ ለዘመናት ተብትቦ የያዛቸውን የመከፋፈል ሰንሰለት የሚበጥሱበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
ይህ በብዙ ዓመታት ጥረት የተገኘ ታላቅ ዕድል በመሆኑ የሁሉም ወገኖች የጋራ አጀንዳና የየግል ኃላፊነት ሲሆን፣ ሁሉም ወገን በውል ተረድቶት በአግባቡ ሊጠቀምበትና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለጋራ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም መንገድ ሊጠርግበት ይገባል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: