Search

በዓይነቱ ልዩ የሆነው የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ልማት

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 64

አዲስ አበባ ከተቆረቆረች 140 ዓመታትን አስቆጥራለች። በእነዚህ ረጅም ዓመታት ጉዞዋ ሸክፋ የመጣችው ውስብስብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሸክም ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። 

የመሰረተ ልማት፣ የፅዳት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ውስብስብ የማኅበረ ኢኮኖሚ ችግሮች አሳስረዋት ምዕተ ዓመቱን የተሻገረች ስሟ ያማረ ውስጧ ግን ብዙ ጉድ የተሸከመ ከተማ ነበረች፡፡

ዛሬ ላይ ግን ይህችን በርካታ ችግሮች የተጫኗትን ግዙፍ ከተማ ወደ ስሉጥ (Smart City) እና ወደ ዘመናዊ ስልጡን የከተማነት ደረጃ ለማሸጋገር እየተደረገ ያለው ጉዞ በየትኛውም መለኪያ እጅግ አስደናቂና ታሪካዊ ነው።

 ይህ ጉዞ የከተማዋን መልክ ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የከተማ ልማት ሳይንስን በተግባር የፈተነ እና በአዲስ መልክ የፃፈ ሆኖ እናገኘዋለን።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የከተማ ልማት ታሪክን ስንመረምር የከተሞች ሁለንተናዊ ዕድገት ብዙ ጊዜ ሚዛኑን የሳተ ሆኖ እናገኘዋለን።

በበለጸጉት ሀገራት ሳይቀር ታላላቅ ከተሞች ሲገነቡ መሰረተ ልማቱ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የዜጎች ህልውና ክፉኛ የተጎዳባቸው አጋጣሚዎች በታሪክ በርካታ ናቸው።

ለአብነት ያህል፣ በአሜሪካ የከተማ ማደስ ፕሮግራሞች ሲተገበሩ አሊያም እንደ ለንደን እና ጄኔቫ የመሳሰሉት ታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች በኢንዱስትሪ አብዮት እና በዘመናዊነት ሽግግር ወቅት ዛሬ ወዳሉበት የዕድገት ማማ ሲወጡ በጊዜው የነበሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ ተፈናቅለዋል፤ ለከፋ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግርም ተጋልጠዋል። 

በእነዚህ የዓለማችን ምርጥ በሚባሉ ከተሞች ታሪክ ውስጥ፣ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ከዜጋ ተኮር ማህበራዊ ፕሮጀክቶች ጋር እኩልና ጎን ለጎን ያስኬዱ መንግሥታት እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው።

ግንባታው እና መስፋፋቱ ቅድሚያ ያገኝ እና ሰብዓዊ ልማት ወደ ኋላየሚከተል ነበር፡፡ አካላዊ ግንባታን ከሰብአዊ ልማት ጋር አጣምሮ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መምራት በምዕራቡ ዓለምም ቢሆን የተለመደና ቀላል አይደለም።

በኢትዮጵያ፣ በተለይም በአዲስ አበባ እየታየ ያለው የልማት ፖሊሲ ግን ከዚህ የተለመደ ታሪክ ፍጹም ያፈነገጠ ልዩ ሞዴል ነው።

በአንድ በኩል ከተማዋ የነበራት አሮጌ ገጽታ ፈርሶ እንደ አዲስ እየተገነባች፣ ታላላቅ የመንገድ፣ የህንጻ፣ ዘመናዊ የአርክቴክቸር ስራዎች፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እና ግዙፍ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የከተማዋ መታደስ እና ፈጣን ዕድገት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ደካማ ዜጎች እንዳይደፈጥጥ፣ የሰዎችን ህይወት የሚታደጉ እና የሚደግፉ ጠንካራ የሰብአዊ ልማት ሥራዎች በከፍተኛ ትኩረት እየተተገበሩ ነው።

ይህ ዓይነቱ ሁለንተናዊ አቀራረብ፣ ከተማዋ ዜጎቿን በእኩል የምትንከባከብ እንድትሆን አስችሏታል። እድገቷ ኮንክሪት እና ህንፃዎችን በማቆም ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን ልጅ ክብር ከፍ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው።

የዚህ ዜጋ ተኮር ፕሮጀክት ተጨባጭ ማሳያዎች በርካታ ናቸው። በምግብ ሥርዓት የትኛውም የከተማዋ ነዋሪ በረሃብ ምክንያት ሕይወቱ እንዳያልፍ በማሰብ በመዲናዋ 30 ግዙፍ የምገባ ማዕከላት ተገንብተዋል።

በእነዚህ ማዕከላት ዜጎች በነጻ ገብተው ይመገባሉ፤ በዚህም መሰረት በየዓመቱም እስከ 600 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ማዕድ ይጋራሉ።

ከዚህም በላይ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ በትምህርት ቤት ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ወላጆች ከጭንቀት፣ ልጆች ደግሞ ከረሃብ ተላቅቀዋል።

ለከተማዋ ዕድገት አስተዋፅዖ የነበራቸው አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች እና ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በልማቱ ሳይረሱ 46 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተው በነጻ ተሰጥተዋቸዋል።

በተጨማሪም በከተማ ግብርና እና በሌማት ትሩፋት ስራዎች 1.2 ሚሊዮን ዜጎች በቤተሰብ ደረጃ ተጠቃሚ በመሆን የኑሮ ውድነትን እንዲቋቋሙ ተደርጓል።

ይህ ነው እንግዲህ እውነተኛው እና የተሟላው የሰብአዊ ልማት ማሳያ። ከዚህ ሰፊ ማኅበራዊ ድጋፍ ጎን ለጎን እየተሳለጠ ያለው ግዙፍ የመሰረተ ልማት እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ከተማዋን ወደ አዲስ የሥልጣኔ ምዕራፍ አሸጋግሯታል።

ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የተተገበረውን የኮሪደር ልማት ብንመለከት ጥቅሙ እጅግ ዘርፈ ብዙ መሆኑን እንረዳለን።

መንገዶች ለተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን ለእግረኛ እና ለብስክሌት ጭምር ምቹ ሆነው ተሠርተዋል፤ ሥነ-ምህዳሩን የሚጠብቁ ሰፊ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችና የሕፃናት መጫወቻዎች ተካትተዋል።

ከዚህም ባሻገር እንደ ሸረሪት ድር የተጠላለፉ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መስመሮች ከመሬት በታች ገብተው 'ስማርት ፖል' እና በዘመናዊ ዲጂታል ሥርዓት መመራት ጀምረዋል።

አስደናቂው የአዲስ አበባ ዳግም መፈጠር በዓለም የከተሞች ልማት ሳይንስ ውስጥ እንደ አዲስ ምዕራፍ ሊወሰድ የሚችል ነው። ምክንያቱም የከተማዋን ምርጥነት እና ውበት የሚያረጋግጠው የሕንፃዎቿ ከፍታ እና የመንገዶቿ ስፋት ብቻ ሳይሆን፣ ለዜጎቿ ያላት ርኅራሄ እና እኩልነትን ያረጋገጠ የልማት ሥርዓት መፈጠሩ ነው።

ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታን ከጠንካራ የማኅበራዊ ድጋፍ ሥራዎች ጋር በሚዛን አጣምሮ መምራት መቻሉ ከተማዋን የሕንፃዎች ክምችት ብቻ ሳትሆን የሕያው ዜጎች እና የሰብአዊነት ተምሳሌት አድርጓታል።

ይህ ሁለንተናዊ፣ ውስብስብ እና እጅግ ፈታኝ ጉዞ አዲስ አበባን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደር የለሽ የሥልጣኔ ማማ ላይ እንድትቀመጥ የሚያደርጋት አኩሪ ገድል ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: