Search

የጨነገፈው የጥፋት ጥምረት - ጽምዶ

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 102

የኢትዮጵያ የማያባራ የልማት ግስጋሴ፣ የብልጽግና ጉዞ እና የተፈጥሮ ጸጋዋን በነጻነት የመጠቀም ሉዓላዊ መብት፣ ከጥንት እስከ ዛሬ ታሪካዊ ጠላቶቿን እና የዘመናት ተላላኪዎቻቸውን ክፉኛ ሲያስጨንቅ እና እንቅልፍ ሲነሣ የኖረ ጉዳይ ነው።

ዛሬም ሀገራችን በሕዝቦቿ ጽኑ አንድነት የዘመናት ስብራቷን ጠግና፣ የተበታተነ አቅሟን አሰባስባ፣ ብሩህ ከፍታዋን ለማረጋገጥ በቆራጥነት ስትነሣ፤ በዙሪያዋ የሚያንዣብቡ አፍራሽ ኃይሎች ይህንን ማዕበላዊ የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ ያልፈነቀሉት ድንጋይ እና ያልሸረቡት ሴራ ፈጽሞ የለም።

ይህንኑ ያረጀ እና ያፈጀ የጥፋት ተልዕኮ ዳግም ለማሳካት "ጽምዶ" የሚል የዳቦ ስም የተሰጠው የጥፋት ስብስብ በማደራጀት ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ለመጎተት ሲሞክሩ ይስተዋላል።

ነገር ግን፣ ጥልቅ በሆነ የፖለቲካ እና የማኅበረሰብ ሚዛን ሲመዘን፣ ይህ ጥምረት ገና ከማኅፀን ውስጥ እያለ የጨነገፈ፣ እውን ሳይሆን ሳይወለድ የመከነ የክስረት ስብስብ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ሐቅ ነው።

በመሠረቱ ይህ "ጽምዶ" ጥምረት ሀገራዊ ራዕይ ኖሮት፣ ወይም በሕዝብ ፍቅር ተገፋፍቶ የተሰባሰበ አይደለም፤ ይልቁንም እርስ በርሱ ክፉኛ የሚጠላላ፣ አንዱ ለአንዱ የጥፋት ምክንያት የሆነ፣ ያለ ደም መፋሰስ እና ያለ ግጭት ሕልውና የሌለው የተቃርኖዎች ክምችት ነው።

በዚህ ጥምረት ውስጥ የታቀፉት የከሰሩ ቡድኖች የሕዝብ አጀንዳ ፈጽሞ የሌላቸው፣ ይልቁንም በገዛ ሕዝባቸው ላይ የተዘረጉ የባዕዳን ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ የባንዳነት ልኡካን ናቸው። የጽንፈኝነት መገለጫ የሆኑ አረመኔያዊ ድርጊቶችን በየጊዜው በመፈጸም፣ የሕዝብን ዕረፍት ሲነሡ የኖሩ ፀረ ሰላም እና ፀረ ሕዝብ ስብስብ በመሆናቸው፣ ኅብረተሰቡ ከኢትዮጵያዊ የሞራል ልዕልና እጅግ ያነሱ እና የወደቁ መሆናቸውን አረጋግጦ ከዕቅፉ ተፍቷቸዋል።

ይህ እኩይ ስብስብ ራሱን በተለያዩ ሕገ ወጥ የንግድ መስመሮች ውስጥ ያስገባ ግልጽ የዘረፋ እና የቅሚያ ኃይል ነው። የራሳቸውን እና የጥቅም ተጋሪዎቻቸውን የማይጠግብ ስግብግብ ፍላጎት ለማሟላት ሲል፣ በሕገ ወጥ የወርቅ እና የተለያዩ ማዕድናት ንግድ፣ በኮንትሮባንድ፣ እንዲሁም በጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ በስፋት የተሰማሩ የሕዝብ ሀብት መዝባሪ ነጋዴዎች ናቸው።

ይህንን የግል ካዝናቸውን የማደለብ እኩይ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሲሉ፣ ምስኪኑን ሕዝብ የንግድ እና የፖለቲካ መነገጃ አድርገውታል፤ ንጹሐንን ከፊት ለጦርነት ለመማገድ እና የግል ጥቅማቸው ጭዳ ለማድረግ ቅንጣት ታክል ወደ ኋላ አይሉም።

አሁን ባሉበት ደረጃ፣ የእነዚህ ኃይሎች ቁመና በየጫካው ከሚንቀሳቀስ ተራ ሽፍትነት የዘለለ አንዳችም ፖለቲካዊ ክብደትም ሆነ ማኅበራዊ መሠረት የሌለው ነው። ከኢትዮጵያ ልማት እና ፍላጎት ውጪ የሆነ፣ የዜጎችን ሰላም እና የሀገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ እና በባንዳነት የተዘፈቀ ይህ ከንቱ ኃይል፣ ረብ የለሽ ነው።

ነገር ግን፣ የትውልዱ እውነታ እና የኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ፍጹም የተለየ ነው፤ ኢትዮጵያ በእነዚህ ትንንሽ የጥፋት ቡድኖች ስጋት ውስጥ ወድቃ አትቀርም፤ ፈጽሞ አትወድቅምም! እነዚህ አቅመ ቢስ፣ በየጫካው በመሽሎክሎክ የሚኖሩ የውጭ ኃይል ተላላኪዎች በተናጠል ቆሙም ሆነ "ጽምዶ" ስም ተደራጁ፣ ለታላቂቱ ኢትዮጵያ ደኅንነትም ሆነ ሕልውና ቅንጣት ታክል ስጋት መሆን የማይችሉ ፍጹም አቅመ አልባዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ግዙፍ ከፍታ እና ጽኑ ሰላም ከእነዚህ ትንንሽ የጥቅም ስብስቦች፣ ከስግብግብ ኮንትሮባንዲስቶች እና በባንዳነት ከተዘፈቁ አቅመ ቢስ የጫካ ሽፍቶች እጅግ በላይ የሆነ ታላቅ ሀገራዊ አጀንዳ ነው።

ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት እና የውስጥ አንድነት በማይናወጥ ዐለት ላይ ገንብታ፣ አልፎም ለቀጣናው ሀገራት የምትተርፍ፣ የአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ የሰላም ሚዛን እና የልዕልና ምሰሶ ናት።

ሰላሟ፣ ልማቷ እና የአብሮነት እሴቷ ከጥቂት ግለሰቦች ኪስ እና ፍላጎት በላይ ነው። የኢትዮጵያን ማዕበላዊ የልዕልና ጉዞ፣ ሳይወለድ የመከነ የጥፋት ጥምረት ለሰከንድም ሊያቆመው አይችልም! አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያን ወደማይቀለበስ የብልጽግና ማማ ማውጣቱን ይቀጥላል!

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: