Search

ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 53

121ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት (አካፓድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ከሐምሌ 8-9 ቀን 2018 . ቤልጅየም መዲና ብራስልስ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ / ሰመሪታ ሰዋሰው የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፏል።

የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የትኩረት አጀንዳዎች የማላቦ ዲክላሬሽን አተገባበር ሂደትን መገምገም፣ የድርጅቱን የፋይናንስ አቅም በዘላቂነት ለመገንባት ስለሚወሰዱ እርምጃዎች መምከር፣ የድርጅቱ ማሻሻያ ሂደት ያለበትን ደረጃ መገምገም፣ የሳሞአ ስምምነትን የትግበራ ሂደት መገምገም እንዲሁም ሌሎች የድርጅቱን እና የአባል ሀገራትን ጥቅም ስለሚያስጠብቁ ጉዳዮች መወያየት ነበር።

ኢትዮጵያ ስብሰባው፣ አቋሟን የሚያንጸባርቁ እና ድርጅቱን በፕሬዚዳንትነት በምትመራበት ወቅት የምትከተላቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች የሚያመለክቱ ንግግሮች አቅርባለች።

በጉባኤው ማጠናቀቂያም ኢትዮጵያ ከኦገስት 1 ቀን 2026 እስከ ጃንዋሪ 31 ቀን 2027 (..) የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆና ተመርጣለች።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ስድስት ወራት የጉባኤው ሰብሳቢነቷ ወቅት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን የትኩረት ጉዳዮች ያስተዋወቀች ሲሆን፣ እነዚህም ከወቅቱ ጂኦፖለቲካዊ እውነታ አኳያ የድርጅቱን /ቤት እና የአባል ሀገራትን የፖሊሲ ነጻነት ማረጋገጥ፣ በራስ አቅም ሊከናወኑ ስለሚችሉ የልማት ሥራዎች እና የሀገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማጋራት በምሳሌነት መምራት፣ በተቋሙ ውስጥ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲጠናከር በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲወገድ መሥራት፣ የድርጅቱ የፋይናንስ እጥረት በዘላቂነት እንዲፈታ የተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እና የአውሮፓ ኅብረት እና የአካፓድ ግንኙነት መሠረት የሆነው የሳሞአ ስምምነት አፈጻጸም በተሻለ መልኩ እንዲጓዝ መሥራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ኢትዮጵያ ድርጅቱ ከተመሠረተ ... 1975 ጀምሮ ሁለት ጊዜ (.. ከነሐሴ 1 ቀን 1986 እስከ ጥር 31 ቀን 1987 እና ከየካቲት 1 ቀን 2017 .. እስከ ሐምሌ 31 ቀን 2017) ተቋሙን በሰብሳቢነት አገልግላለች።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆና መመረጧ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ፈጣሪነት በድጋሚ የሚያረጋግጥ ታላቅ ስኬት ነው።

ይህ ታሪካዊ ኃላፊነት ሀገራችን በደቡብ-ደቡብ ሁለንተናዊ ትብብር ላይ ያላትን ተሳትፎ ይበልጥ ከማጠናከሩ ባሻገር፣ ከአባል ሀገራቱ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የሚደረጉ ትብብሮችን በበላይነት ለመምራት፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እና መልካም ገፅታዋን ለመገንባት የዲፕሎማሲ ዕድሎችን ይከፍታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ለኖቬምበር 2026 . የታቀደው 122ኛው የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት አዲስ አበባ እንዲካሄድ በድርጅቱ አባል ሀገራት ተወስኖ ጉባኤው መጠናቀቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: