ለዘመናት ፀጥ ብሎ በነበረው የኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ያልተለመደ የሞተር ድምጽ አስተጋባ።
አንዲት የፈረንሳይ አውሮፕላን የሀገራችንን ሰማይ ሰንጥቃ ስታልፍ፣ በወቅቱ ድምፁን የሰማው ሁሉ ማለቂያ ለሌለው እና አፍሪካን ለሚያኮራ ታላቅ ሀገራዊ የከፍታ ህልም መወለድ ምክንያት መሆኑን አልተገነዘበም ነበር።
ይህ የዘመናዊ አቪዬሽን ብልጭታ በቢሾፍቱ ሐረር ሜዳ ከተለኮሰ በኋላ ህልሙ ወደ እውነት ተቀይሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በይፋ የተመሰረተው ታህሳስ 12 ቀን 1938 ዓ.ም ነበር።
ተቋሙ ከተመሰረተ ከጥቂት ወራት በኋላ መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም በአምስት ‘ሲ-47' የጦር አውሮፕላኖች የመጀመሪያ በረራውን ወደ ካይሮ በማድረግ ዛሬ ላይ ለደረሰበት ማያቋርጥ የልህቀት ጉዞ ጅማሮውን አበሰረ።
አየር መንገዱ 80ኛ ዓመቱን በክብር ሲያከብር፣ ታሪኩ የአንድ የንግድ ተቋም ስኬት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የነፃነት እና የአንድነት ተምሳሌት ጭምር መሆኑን እንረዳለን።
በ1950ዎቹ አፍሪካውያን አህጉራቸውን በቅጡ መጎብኘት ባልቻሉበት አስቸጋሪ ዘመን፣ አየር መንገዳችን የምሥራቅ እና የምዕራብ አፍሪካን ሰማይ በማስተሳሰር ፈር ቀዳጅ ሆኗል።
ከዚህም ባሻገር የአፍሪካ መሪዎችን በአዲስ አበባ በማሰባሰብ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) መመስረት ያበረከተው ታሪካዊ አስተዋጽኦ፣ አፍሪካ የራሷን እጣ ፈንታ መወሰን እንደምትችል ለዓለም በተግባር ያረጋገጠበት ደማቅ ማሳያ ነው።
በቴክኖሎጂ እና በአዳዲስ ግኝቶች ቀዳሚ በመሆን አቻ የማይገኝለት አየር መንገዳችን፣ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂን ወደ አፍሪካ በማምጣት ረገድ ሁሌም ግንባር ቀደም ነው።
በዘመኑ አዲሱን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን በመገንባት የመጀመሪያውን ጄት (ቦይንግ 720-ቢ) በአፍሪካ ምድር ያበረረው እሱው ነበር።
ወደ ቻይና በመብረርም ከአፍሪካ ቀዳሚው ሲሆን፣ በ2004 ዓ.ም የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላንን ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ከጃፓን በመቀጠል ሁለተኛ በመሆን በማስገባት የሰማይ ላይ ንግሥናውን በቴክኖሎጂ አጽንቷል።
በ1964 ዓ.ም ኮሎኔል ስምረት መድኃኔን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ከሾመበት ጊዜ አንስቶ፣ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ በሀገር በቀል ባለሙያዎች እየተመራ ከትውልድ ወደ ትውልድ በስኬት እየተሸጋገረ ይገኛል።
ተቋሙ በፈተና የማይበገር ብረት መሆኑን በጉልህ ካሳየባቸው አጋጣሚዎች አንዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ነበር።
ዓለም በራፎቿን ዘግታ በነበረበት በዚያ አስከፊ ጊዜ፣ የአየር መንገዱ አመራሮች በፈጠራ በታከለበት ፍጥነት የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ወደ ጭነት አስተላላፊነት በመቀየር ሕይወት አድን መድኃኒቶችን እና የህክምና ቁሳቁሶችን ለዓለም አዳረሱ።
ይህ ተግባሩም አፍሪካውያንን ያኮራ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የታደገ እና ዓለምን ያስደነቀ ታሪካዊ ጀብዱ ሆኖ በወርቅ ቀለም ተጽፏል።
የአየር መንገዱ ስኬት በተለይ ባለፉት ስምንት ዓመታት እጅግ የአስገራሚ ጉዞውን ከፍታ አሳይቷል።
ተቋሙ ያቀደውን "ራዕይ 2025" ከዓመታት በፊት በማሳካት አሁን ላይ አድማሱን በማስፋት ወደ "ራዕይ 2035" የልህቀት ጉዞ ተሸጋግሯል።
የ"ስካይትራክስ"ን ሽልማት ለተከታታይ ዓመታት በማሸነፍ፣ የ"ስታር አላያንስ" አባል በመሆን ከ135 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እያካለለ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት ከ140 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የያዘ ሲሆን፣ በቅርቡ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የ'ኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል'ን በማስፋፋት፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲን በማሳደግ እና የኢ-ኮሜርስ አገልግሎት በመጀመር ራሱን ወደ ግዙፍ የአቪዬሽን ኮንግሎሜሬት (ሁለንተናዊ የንግድ ስብስብ) አሳድጓል።
ይህ ሁሉ ስኬት በአጋጣሚ የመጣ አይደለም። የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገልጹት፣ የተቋሙ ዋነኛ የስኬት መሰረት ጠንካራ የፋይናንስ ዲስፕሊን፣ በሰው ኃይል እና በአሠራር ሥርዓት ላይ የተገነባ ጽኑ መሰረት ነው።
አየር መንገዱ ትናንት ታሪኩን ከጀመረባት ከቢሾፍቱ አጠገብ፣ በቅርቡ በአፍሪካ ትልቁን እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ የሜጋ አውሮፕላን ማረፊያ እየገነባ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ተቋማትን መስርተው በዓለም አቀፍ ደረጃ በልህቀት መምራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
የ80 ዓመታት የልህቀት እና የትስስር ጉዞው ዛሬም ወጣት በሆነ መንፈስ ቀጥሏል። ለሀገር ኢኮኖሚ እና ለአፍሪካ ዕድገት ፋና ወጊ ሆኖ የጀመረው ይህ ጉዞ ማብቂያ የለውም፤ ምክንያቱም መነሻውን እንጂ መድረሻውን የወሰነ ተቋም አይደለምና!
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: