Search

ከወጣቶች አዲስ ዕይታ እስከ አንጋፋዎች ልምድና ጥበብ፣ ሁሉንም ያካተተው የሀገራዊ ምክክር ማዕድ

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 53

ከትናንት በስቲያ በይፋ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር፣ የኢትዮጵያን  ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አካታች መድረክ መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው።

ይህ ታሪካዊ ምክክር ማንነትን መሠረት ያደረገ ምንም ዓይነት ገደብ ሳያደርግ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች እያሳተፈ ያለ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ነው።

የፆታ ሚዛናዊነትን ብንመለከት፣ ምክክሩ የወንዶችን እና የሴቶችን ድምፅ በእኩልነት ለማስተናገድ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።

ከሁሉም ክልሎችና የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ ሴቶች፣ እናቶች እና ወጣት ሴት መሪዎች በምክክሩ በቀጥታ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ይህም ማለት ሀገራችንን የተመለከቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ለጉባኤው በሚቀርቡበት ወቅት፣ የሴቶች እይታና ፍላጎት በእኩል ደረጃ ይስተናገዳል።

ዕድሜን ያማከለ ውክልና በማረጋገጥ ረገድም መድረኩ የአዛውንቶችን ጥበብ እንዲሁም የወጣቶችን ጉልበት እና አዲስ ዕይታ በአንድ ጣራ ሥር አገናኝቷል።

የወደፊቷን ኢትዮጵያ የሚረከቡ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች በምክክሩ ሂደት የራሳቸውን አሻራ እያኖሩ ነው።

የሀገር ሽማግሌዎችና አንጋፋ ምሁራንም ካላቸው የካበተ ልምድ ለሀገራዊ ሰላም ግንባታ የሚበጁ ምክረ ሀሳቦችን ለጉባኤው የሚያጋሩበት ሰፊ ዕድል አላቸው።

በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አካላዊ ወይም ሌላ ማንነት ላይ መሠረት ያደረገ ምንም ዓይነት ገደብ የማያደርግ መሆኑ የሀገራዊ ምክክሩ ልዩ መገለጫው ነው።

ለአብነትም፣ አካል ጉዳተኞች ያለምንም መድልዎ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በምክክሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል።

ከሁሉም ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር በቀል እውቀት ባለቤቶችና የሁሉም ብሔረሰቦች ተወካዮችም የመድረኩ ተሳታፊ ናቸው።

ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ለማስቻል፣ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሁሉ ወገኖች ያለምንም ገደብ በምክክሩ እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል።

ይህ ታሪካዊ መድረክ፥ ኢትዮጵያ ያሉባትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት የምትችለው፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ ሀገራዊ ምክክር  ሲደረግ ብቻ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ነው።

በተጨባጭም መድረኩ አንዳችም ዓይነት የማንነት ገደብ ሳያደርግ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የባለቤትነት ስሜት በመፍጠር ከመጨረሻው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: