Search

ፈተናን ወደ ስኬት ያሻገሩ አምስት የተግባር ዓመታት

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 57

ኢትዮጵያ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ያጋጠሟትን ውጫዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች በጽናት ተቋቁማ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዋን ወደ ላቀ ደረጃ ካሸጋገረች አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ይህ ጊዜ ሀገራችን ከከባድ የሕልውና አደጋ ወጥታ ወደ ጸና የልማት ምዕራፍ የተሸጋገረችበት የታሪክ መስቀለኛ መንገድ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን ድምፅ ማግኘቱን ተከትሎ፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሕዝብ የሰጠውን አደራ ተቀብለው ሀገር የሚቀይር ሥራ ለመሥራት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፓርቲያቸው ለሕዝብ የገቡትን ቃል መሠረት በማድረግም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳቸው የጎላ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶችን አስመዝግበዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ዕድገት

በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ገበያውን ነፃ በማድረግ በጥቁር ገበያ እና በሕጋዊ ባንኮች መካከል 100 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረውን ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ማጥበብ ችሏል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ማስመዝገብ ችላለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ወለድ ተኮር የገንዘብ ፖሊሲ በመሸጋገር መንግሥት ከማዕከላዊ ባንክ የሚወስደውን ቀጥታ ብድር ማቆሙ ሌላው ዐቢይ እርምጃ ነው።

ይህ ውሳኔ በሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቦ የነበረውን የዋጋ ንረት 34.5 በመቶ ወደ ባለ ነጠላ አኃዝ ዝቅ ለማድረግ አስችሏል።

ይህ ታሪካዊ የሪፎርም ስኬት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) 3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር ማዕቀፍ ያስገኘ ሲሆን፣ በተገባደደው በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ዕድገት 10.2 በመቶ እንደሚሆን ተተንብዩዋል።

ከሕዳሴው ግድብ እስከ ጉባ ብሥራት

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አምስተኛውን እና የመጨረሻውን ዙር የውኃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ፣ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም ላይ በመድረስ ጳጉሜን 2017 . በይፋ ተመርቆ ሙሉ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በግድቡ ምረቃ ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "የጉባ ብሥራት" ፕሮጀክቶችን አውጀዋል

ከእነዚህ የጉባ ብሥራቶች መካከልም የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ እና ጋዝ ማጣሪያ፣ እንዲሁም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታቸው ተጀምሮ ሌሊት እና ቀን እየተካሄደ ይገኛል።

የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፣ ይህንኑ ለማስፈጸም የኢትዮጵያ ኑክሌር ኃይል ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

የከተማ ልማት እና ቱሪዝም

በከተማ ልማት ዘርፍ በአዲስ አበባ የተጀመረው የከተማ ኮሪደር ልማት፣ ከተማዋን ለኑሮ ምቹ እና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ሆኖ ተሞክሮው ወደ ክልል ከተሞች ተስፋፍቷል።

በዚህ የከተማ ማዘመን ሒደት ውስጥ የጉባ ብሥራት አካል የሆነው 1.5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዓለም አቀፍ አዳራሽ በማካተት ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል አድርጓታል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ጊዜ 10 ሺሕ በላይ ሰዎችን የሚያሳትፉ ግዙፍ ጉባኤዎችን ማስተናገድ የሚችለው አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ወደ ሥራ ገብቷል።

እንደ "የጫካ ፕሮጀክት" ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነቡ ሲሆን፣ "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" የተሠሩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች የዘርፉን ዕድገት አፋጥነዋል።

ዲፕሎማሲ፣ ግብርና እና አረንጓዴ ዐሻራ

ስኬታማው የሕዳሴ ዲፕሎማሲያችን ከታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የነበረውን ውጥረት ከማርገቡም ባለፈ፣ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ትሥሥራችንን አጠናክሯል።

ከዚህ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ታሪካዊ በሆነ ውሳኔ የብሪክስ አባል መሆኗ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷን እና የኢኮኖሚ ትሥሥሯን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።

በሀገር ውስጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሰፊ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጭ የምግብ ዕርዳታ ጥገኝነት ተላቅቃ ዓመታዊ ምርቷን 33 ሚሊዮን ቶን በማድረስ በአፍሪካ ቀዳሚ አምራች ሆናለች።

"ሌማት ትሩፋት" መርሐ ግብርም የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ጉልህ መሻሻል ታይቷል።

በተጓዳኝም ባለፉት ሰባት ዓመታት 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል የሀገራችንን የደን ሽፋን 23.6 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል።

ለዚህ ሁሉ ስኬት መሠረት የሆነው ደግሞ በፕሪቶሪያው ስምምነት የተረጋገጠው እና ሀገራዊ ሰላምን ያሰፈነው ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ነው።

የተቋማት ግንባታ፣ ዲጂታላይዜሽን እና ሀገራዊ መግባባት

ሀገርን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም በተደረገው የሪፎርም ሥራ፣ 47.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች "ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ሆነዋል። እንዲሁም 41 የፌዴራል ተቋማትን በአንድ ያገናኘው "መሶብ" መተግበሪያ የአገልግሎት አሰጣጥን በእጅጉ አቅልሏል።

ለአንድ ሀገር ጸንቶ መቆም አስፈላጊ በሆኑት የጸጥታ ተቋማት ውስጥ የተተገበረው ሪፎርም፣ ዜጎች የሚኮሩባቸው እና የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚፈሯቸው ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡ አድርጓል።

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ዘርፍ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራችን 93 በመቶ አካባቢዎች አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ዋናውን ጉባኤ በይፋ ጀምሯል።

የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችለው ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጸድቆ የተሟላ የፍትሕ ሥርዓትን ለማስፈን ዝግጁ ሆኗል።

ሌብነት እና የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የንብረት ማስመለስ አዋጅ ወጥቶ ወደ ተግባር ገብቷል።

በየጊዜው አቅሙን እያጠናከረ የመጣው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 . ያካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተቋማት ግንባታችን ሕያው ማሳያ ነው።

እነዚህ እውነታዎች በግልጽ የሚያሳዩት የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በርካታ ውስብስብ ፈተናዎችን በጽናት አልፎ ዛሬ ላይ በተጨባጭ ሀገራዊ ስኬቶች መታጀቡን ነው።

የተጀመሩት ሁለንተናዊ የሪፎርም እና የልማት ሥራዎች አሁን ባለው የላቀ ቁርጠኝነት ተጠናክረው ከቀጠሉ፣ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ምዕራፍ ብሩህ፣ የበለጸገ እና የዜጎቿን የዘመናት የልማት ጥማት በዘላቂነት የሚያረካ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: