Search

ከጎረቤት ሀገራት ተነስቶ እስያ የደረሰው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ዲፕሎማሲ

ቅዳሜ ነሐሴ 10, 2017 127

ፓኪስታን ለገባችበት የአየር ንብረት ለውጥ ችግር  የኢትዮጵያን አረንጓዴ ዐሻራ ተሞክሮ  ሁነኛ መፍትሄ አድርገው እንደሚስዱት የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ከተለያዩ  የኢትዮጵያ ክልላዊ መሥተዳድሮች የተወከሉ ወጣት አደረጃጀቶች የልዑካን ቡድን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በካራቺ ባሰናዳው ዝግጅት ላይ ተገኝተው አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል  በከር (ዶ/ር) በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ በጎረቤቶቿ የጀመረችውን የአረንጓዴ ዐሻራ ዲፕሎማሲ አስፍታ  በፓኪስታን ሶስት ታላላቅ ከተሞች የችግኝ ድጋፍና ተከላ በማካሄድ ትስስሩን ወደ እስያ የወንድማማችነትና የትብብር ማጠናከሪያ መድረክ አሳድጋዋለች ብለዋል።

በተለይም የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን እየተጋፈጠች ላለችው ፓኪስታን የኢትዮጵያ ተሞክሮ ቀርቦ በቀጣይም በትብብር መሥራት  እንደሚፈልጉ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያ ልዑክ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ  የአረንጓዴ ዐሻራ ዳያሎግ  የወጣቶች ልዑካን ቡድን መሪ እና የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈዲላ ቢያ፥ በፓኪስታን የተከልነው የሁለቱን አገራት ወንድማማችነት የሚያጸና ዲፕሎማሲ አብነታዊ ተልዕኮ ነው ብላለች።

የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ያለፉት 7 ዓመታት የዘርፉ ተሞክሮ እና የመጣው ለውጥ ፓኪስታንን ጨምሮ ዓለም ሊማርበት የሚገባው ውጤት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በሰዒድ ዓለሙ

#EBCdotstream #Ethiopia #Pakistan #GreenLegacy #GreenDiplomacy