አሰብ ለኢትዮጵያ የጂኦግራፊያዊ ቁመናዋ፣ ተፈጥሯዊ ድንበሯ እና የኅልውናዋ ትንፋሽ ናት። የተፈጥሮን አቀማመጥ በጥልቀት ስንመለከት፣ ግዙፉ የኢትዮጵያ ተራራማ መልክዓ ምድር ቁልቁል ተንከባሎ የሚያርፈውና የየብሱን ጉዞ አጠናቅቆ ከዓለም አቀፉ የውሃ አካል ጋር የሚገናኘው በቀይ ባሕር ዳርቻ በተለይም በአሰብ ወደብ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ወንዞች ሳይቀሩ ፊታቸውን ወደዚሁ ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፍ የሚያዞሩ መሆናቸው፣ ይህ ተፈጥሯዊ ትስስር አሰብን የኢትዮጵያ የዕድገት፣ የብልጽግና እና የሉዓላዊነት ተፈጥሯዊ በር ያደርጋታል።
ከታሪካዊ ማስረጃዎች እና እውነታዎች አኳያ ስንቃኘው፣ አሰብና ኢትዮጵያ ፈጽሞ ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ አካል ሁለት ገጽታዎች ሆነው ኖረዋል። አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ይዞታና ድንበር ሲያስረዱ አሰብን እና የባሕር ዳርቻውን የሚያካትት መሆኑን ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት በግልጽ ይመሰክራሉ።
በዚህ ታሪካዊ ደብዳቤያቸው አፄ ምኒልክ የጥንት ዜጋቸው የነበረውን የሱልጣን መሐመድ ሃንፍሬን ግዛት ሙሉ በሙሉ ይዞ በባሕር ዳር አረፋሊ እንደሚደርስ አረጋግጠዋል። ከዚህም ባሻገር፣ የቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ያለው ጥልቅ የታሪክ፣ የደም፣ የባህል እና የሥነ-ልቦና ትስስር አሰብን ከእናት ሀገሯ ከኢትዮጵያ ነጥሎ ማየት ተፈጥሮን እንደመጋፋት የሚቆጠር መሆኑን በተግባር ያረጋግጣል።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ቢሆን፣ ይህንን ተፈጥሯዊ ትስስር አምኖ ተቀብሎት ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በውሳኔ ቁጥር 390 (V) ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ሲያስተሳስር፣ ዋነኛ መነሻ ካደረጋቸው ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ተገቢና ሕጋዊ የባሕር በር ጥያቄ በአሰብና በምጽዋ በኩል አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ነበር። ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ ከባሕር ጠረፉ ጋር ያላትን የጂኦግራፊ፣ የኢኮኖሚ እና የዘር ትስስር በሚገባ ያገናዘበ ፍትሐዊ እርምጃ ነበር።
በዘመናዊ ታሪክም ቢሆን፣ አሰብ ከባዶ ተነስታ በአፄ ኃይለሥላሴና በደርግ መንግሥታት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባት ለመሃል ሀገር ኢኮኖሚ ማስተላለፊያ እንድትጠቅም ተደርጋ ያደገች የኢትዮጵያ ብቸኛ የተፈጥሮ ወደብ ነች። በጂኦግራፊያዊ ቅርበት ረገድ አሰብ አሁን ካለው የኢትዮጵያ ድንበር በግምት 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ብቻ የምትገኝ ስትሆን፣ ይህ አጭር ርቀት ገቢና ወጪ ንግድን እጅግ ፈጣን እና ዋጋ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል ወደር የለሽ የተፈጥሮ ስጦታ ነው።
አሰብ የኢትዮጵያ የብልጽግና እና የዕድገት በር መሆኗን በግልጽ የሚያሳየው የኢኮኖሚው ሀቅ ነው። ታዋቂው የኢኮኖሚ ልማት ሊቅ ፖል ኮሊየር "የመጨረሻዎቹ ድሃ ቢሊዮኖች" በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ የባሕር በር ካለህ ገበያህ መላው ዓለም ሲሆን፣ የባሕር በር ከሌለህ ግን ገበያህ ጎረቤት ሀገር ብቻ በመሆኑ ወደብ አልባ ሀገራት የጎረቤቶቻቸው እስረኞች ናቸው።
ሌላው የኢኮኖሚ ምሁር ጄፈሪ ሳክስም በበኩላቸው፣ የወደብ አልባነት አንዱና ዋነኛው የኢኮኖሚ ችግር የሀገርን ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ትስስር ማግለልና በሌሎች ተጽዕኖ ስር መውደቅ መሆኑን በስፋት ያብራራሉ። ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ወደብ አልባ መሆን ብቻ የአንድን ሀገር የውጭ ንግድ መጠን ከ33 በመቶ እስከ 43 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ትልቁ የባሕር በር አልባ ሀገር በመሆኗ "በጂኦግራፊ እስር ቤት" ውስጥ ወድቃለች። የገዛ የተፈጥሮ በሯን አሰብን ባለመጠቀሟ ምክንያት ብቻ በየዓመቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ወይንም በቀን ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ ኪራይ እና ለትራንዚት ወጪ ትከፍላለች። ይህ ከፍተኛ "የወደብ አልባነት ግብር" የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ከማሟጠጡም በላይ፣ የዜጎችን የቀን ተቀን የኑሮ ውድነት በማባባስ እና የወጪ ንግዷን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆን በማድረግ ትልቅ የዕድገት ማነቆ ሆኖበታል። አሰብ የተፈጥሮ በሯ ሆኖ ቢያገለግል ኖሮ፣ ይህ ሁሉ ሀብት ለሀገር ውስጥ ልማት፣ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ለዜጎች የኑሮ መሻሻል ይውል ነበር።
አሰብና ኢትዮጵያ ፈጽሞ ሊነጣጠሉ የማይችሉ፣ በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ እና በኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በጥብቅ የተሳሰሩ ህያዋን አካላት ናቸው። አሰብ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኞት ወይም የቅንጦት ጉዳይ ሳትሆን፣ የኢኮኖሚ ነጻነት ማረጋገጫ፣ የወጪ ንግድ ማሳለጫ እና የወደፊት የብልጽግና ትንሣኤ ቁልፍ ናት።
ወደብ አልባነትን አሸንፎ ወደ ብልጽግና ማማ ለመውጣት፣ ኢትዮጵያ ይህንን ተፈጥሯዊና ቅርብ በሯን ተጠቅማ ከዓለም ጋር ያለምንም ከልካይ መገበያየት መቻል አለባት። አሰብ፣ ያች የተፈጥሮ በር ዳግም ስትከፈት የኢትዮጵያ እውነተኛ የኢኮኖሚ ታላቅነት እና ቀጣናዊ ሞገስ በተሟላ ሁኔታ ይረጋገጣል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: