Search

ተዋስዖ መር ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 56

ዴሞክራሲ የብዙኃን አስተዳደር መሆኑ ቢታመንም፣ ሰፊ ብዝኃነት፣ የባህል እና የቋንቋ ስብጥር ባላቸው ኅብረ ብሔራዊ  ሀገራት ውስጥ የአብላጫ ድምፅ መርህን ብቻ መከተል ወደ “ብዙኃን ጭቆና” (Tyranny of the majority) ሊያመራ ይችላል። ይህንን የፖለቲካ አደጋ ለማስቀረትና ማኅበረሰባዊ ግጭትን በመከላከል የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት "የመግባባት ዴሞክራሲ" ወደር የለሽ ጽንሰ-ሐሳባዊና ተግባራዊ ፋይዳ አለው።

የመግባባት ዴሞክራሲ መሠረታዊ ባህሪው ሥልጣንን ማጋራት፣ ማከፋፈልና አካታችነትን ማረጋገጥ ነው። ይህ ሥርዓት በአምስት አንኳር ምሰሶዎች ይተነተናል።

አንደኛው “የላቀ ትብብር ወይም ታላቅ ቅንጅት” (Great Coalition) ሲሆን፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን የሚወክሉ  ልሂቃን በተለያየ ሁኔታ በሀገራዊ ጉዞ በጋራ እና በትብብር የሚሳተፉበት አሠራር ነው።

ሁለተኛው “አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰቦች ጥበቃና የመሻር መብት” (Minority Protection and Mutual Veto) ነው። ይህ መርህ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰቦች ድምፃቸው እንዳይዋጥና መሠረታዊ ጥቅማቸው በብዙኃኑ ድምፅ እንዳይረገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ከለላ የሚሰጥ ነው።

ሦስተኛው “የተመጣጣኝ ውክልና” ሲሆን፣ በፓርላማ፣ በሲቪል ሰርቪስና በበጀት ክፍፍል ፍትሐዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተሳትፎን ያረጋግጣል።

አራተኛው “ራስን በራስ ማስተዳደር” ሲሆን፣ ማኅበረሰቦች በቋንቋ፣ በባህል እና በትምህርት ዘርፍ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲወስኑ ያደርጋል።

አምስተኛውና ይህንን ሞዴል ይበልጥ አካታች የሚያደርገው ደግሞ “የአደባባይ ተዋስኦን ማበረታታት” (Public Deliberation) ነው። ተዋስኦ መር ዴሞክራሲ ዜጎች በምክንያታዊ ክርክርና ሕዝባዊ ውይይት ውስጥ ገብተው ውሳኔዎች የጋራ ቅቡልነት እንዲያገኙ ያደርጋል።

እነዚህ ጽንሰ-ሐሳባዊ የመግባባት ዴሞክራሲ መለያዎች ከኢትዮጵያ ሥነ-ተፈጥሮና ፖለቲካዊ አውድ ጋር ጥልቅ ቁርኝት አላቸው። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓቷ ሁሉንም ድምፆች በእኩልነት ማስተናገድ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በአብዛኛው በአሸናፊና ተሸናፊ  ቀመር ላይ የተገነባ በመሆኑ፣ የተማከለና አግላይ ሥርዓት ብዝኃነትን እንደ ስጋት በመቁጠሩ ሀገራችንን ለተደጋጋሚ ግጭቶችና የእርስ በርስ ጦርነቶች ዳርጓታል። ያለፉት የአዋሃጅ (Integrationist) ዴሞክራሲ ሙከራዎች ማኅበረሰባዊ ማንነትን በማግለላቸው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ፈጥረው አልፈዋል።

የመግባባት ዴሞክራሲ ግን ይህንን ታሪካዊ ስብራት ለመጠገን ፍቱን መፍትሔ ነው። የላቀ ትብብርን (Great Coalition) መተግበር የኢትዮጵያን የፖለቲካ ልሂቃን ከዜሮ-ድምር የፉክክር ፖለቲካ አውጥቶ በሀገር ግንባታ ላይ በጋራ እንዲሠሩ በማድረግ የፖለቲካ መረጋጋትን በዘላቂነት ያሰፍናል።

በተጨማሪም፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ማኅበረሰቦች መብት መጠበቅ  በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የማንነት ፖለቲካ ውጥረት በማርገብ፣ እያንዳንዱ ዜጋና ብሔር በሀገሩ እኩል ባለቤትነት እንዲሰማው ያደርጋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰቦች ከባህል፣ ከቋንቋ ወይንም ከፖለቲካ ውክልና አንፃር ሊገለጹ ይችላሉ። በመሆኑም የእነዚህን ቡድኖች መብት በተመጣጣኝ ውክልናና ራስን በራስ በማስተዳደር መብት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው። ይህ አካታችነት ከህዳጣን አግላይነት (Marginalization) ስሜት የሚመነጩ ማኅበራዊ ቅራኔዎችንና ግጭቶችን ቀድሞ በመከላከል ዘላቂ አዎንታዊ ሰላምን ያሰፍናል።

ከምንም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ የተዋስኦ ዴሞክራሲን  ማበረታታት ያለው ፋይዳ ወደር የለውም። የአደባባይ ተዋስኦ ዴሞክራሲን ከልሂቃን ድርድር ባሻገር ወደ ሰፊው ሕዝብ በማውረድ “መሠረታዊ አካታችነትን” (Substantive inclusion) ያረጋግጣል።

በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የዚህ ተዋስኦ አንዱ መገለጫ ሲሆን፣ የተካረሩ የፖለቲካ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በምክንያታዊ የሐሳብ ልውውጥ ለመፍታት፣ ሁሉን አቃፊ የጋራ ትርክትን (Civic Nationalism) ለመገንባት እና ጠንካራ ብሔራዊ መግባባትን ለማፅናት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው።

መግባባት በመግባባት ዴሞክራሲ ውስጥ ዕውን የሚሆነው ጽንሰ-ሐሳቡን ወደ ሀገራዊ መሬት በማውረድ ነው። የመግባባት ዴሞክራሲ ትግበራ ስኬት በዋነኝነት የሚወሰነው የፖለቲካ ልሂቃን የፖለቲካ ተሳትፎ ማነቆዎችን ለመፍታት በሚያሳዩት ቁርጠኝነት ላይ ነው። ስለዚህም፣ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የባህልና የማንነት ብዝኃነት ተጠቅማ ጠንካራ እና የፀናች ሀገረ-መንግሥት መገንባት የምትችለው፣ የህዳጣንን ድምፅ የሚጠብቅ፣ የላቀ ትብብርን የሚፈጥር እና ሕዝባዊ ተዋስኦን የሚያበረታታ ሥርዓት ስትተገብር ብቻ ነው። ይህ ሥርዓት ብዝኃነት ባለባቸው ሀገራት ግጭትን ለመከላከል ድልድይ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: