Search

የትሮይ ፈረስ፡- የከሰረው የህወሓት ቡድን የቀጠለ የባንዳነት ቁማር

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 120

ታሪክ በተደጋጋሚ የሚያስተምረን አንድ ሸንቋጭ እውነት አለ። ባንዳነት የተለያየ መልክና አይነት አለው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ባንዳነት ብዙ መልክና ገፅታ የነበረው የታሪካችን ጥቁር ጠባሳዎች ናቸው፡፡ ትናንት ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ስትወረር በትንንሽ ሹመትና ድለላ የሀገራቸውን ተራራ እና ቁልቁለት፣ ዋሻና ጉድጓድ ለፋሺስት ከፊት ከፊት ሆነው እየመሩ እየጠቆሙ አርበኞችን ያስፈጁ ባንዶች ለታሪክ ፍርድና ለህሊና ሚዛን በታሪክ ማህደር ተከትቧል፡፡

ዛሬም በምስራቅ አፍሪካና በዓባይ ተፋሰስ፣ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ተመሳሳይ የባንዳነት ግዥና የሸፍጥ ስትራቴጂ ተቀነባብሯል። የዘመናችን የባንዳነት የትሮይ ፈረስ ደግሞ "ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን" ነው። ይህ የከሰረ ቡድን ለጠላት የማደር፣ ራስን አሳልፎ የመሸጥ፣ በልዩነት የመኖርና የጥላቻ ሰባኪነት ወኪል ነው፤ ለታሪካዊ ጠላቶች በሎሌነትና በባንዳነት ማገልገል የሚወደስበት የውርደት ትርክት ተራኪ ቡድን ነው።

ሕገ-ወጡ  ቡድን ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር የሚፈጥረው ጥምረት የፖለቲካ ራዕይ ወይም የዓላማ አንድነት ያለው ስብስብ አይደለም። ይልቁንም "የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው" በሚል መርዛማ የዜሮ ድምር ፖለቲካ የተጠፈነገ ነው። እርስ በእርሱ የሚጠላላ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ብቻ የተጋባ የጥፋት ኃይሎችን በዙሪያው የሰበሰበ የሴራ ማዕከል ነው።

ከታሪካዊ የውጭ ጠላቶች እስከ ሀገር ውስጥ ጽንፈኞች የተዘረጋው የዚህ ቡድን የሴራ ሰንሰለት፣ ገና ከጅምሩ የከሸፈ የጥፋት ፅንስ ነው። ይህ የከሰረ የህወሓት ቡድን የትናንቱን የታሪክ ትምህርት የዘነጋ፣ ራሱን ለባዕዳን ገበያ በገዛ ፈቃዱ ያቀረበ የዘመኑ የባራቲየሪ ተላላኪ ነው። ይህ ኃይል የፖለቲካ ራዕይ ያለው ሳይሆን፣ ያበጠ የግል ኢጎውን ለማስታገስ ብቻ ሀገር የሚሸጥ፣  ርካሽ የፖለቲካ ድንክ ነው። መላላክና የባዕድ አጀንዳ አስፈፃሚነት ተፈጥሯዊ መልኩና የተፈጠረበት እኩይ ዲኤንኤ ነው።

ይህ አጥፊ ቡድን የሕዝብ ዓላማ የለውም። በቀላሉ የማይረካ የስልጣን ጥማቱን ለማስታገስ ብቻ ራሱንና ግብረ-አበሮቹን እንደ ርካሽ ሸቀጥ ለባዕዳን ገበያ ያቀረበ፣ ጌታው ባዘዘው ልክ በማንም የሚጋለብ የዘመናችን የትሮይ ፈረስ ነው ሲሆን፣ ለታወረ የሥልጣን ጥማቱ ሲል ሀገርን በቁማር መሸጥ፣ የገዛ ወገኑን ማስፈጀት አንዳች የማይሰቀጥጠው የክህደት ማሳያ ነው።

ይህ ቡድን የተጠናወተው የባንዳነት ልክፍት ዛሬ በድንገት የጀመረ አይደለም። ታሪክ ቁልጭ አድርጎ እንደሚመሰክረው፣ ይህ አካል ትናንት ሥልጣን ተቆናጦ ሀገር ይመራ በነበረበት ጊዜም እንኳ፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ሲያገለግልና ጥቅሟን አሳልፎ ሲሰጥ የኖረ ነው። ለባዕዳን መላላክና አጀንዳ አስፈፃሚነት ተፈጥሯዊ መልኩ ነው። ሥልጣን ላይ ሲሆን ሀገር ይሸጣል፣ ከሥልጣን ሲወርድ ደግሞ ከሌሎች ባንዶች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ ይማማላል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቅርቡ በሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ምርቃት ላይ እንዳጋለጡት፣ ይሄ አዲስ ክስተት አይደለም። የ1960ዎቹ የባዕዳንና የባንዳ ጋብቻ ቀጣይ ምዕራፍ ነው። ያኔ፣ “ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም”ን ካባ አድርጎ የተነሳው ይህ የጥፋት ኃይል፣ ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ከባሕር በር አባረረ፤ ሀገራችንን በእርስ በርስ ጦርነት አዳከመ። ያኔ የፈርዖን ተላላኪዎች ስኬት ያገኙት ጀግና ስለነበሩ አይደለም፤ የገዛ ሀገሩን የሚወጋ እንደ ህወሓት ያለ “የውስጥ ባንዳ” ስላገኙ እንጂ! ዛሬም ያ የባንዳነት ታሪኩን በአዲስ ሸፍጥ ለመድገም እየሞከረ ነው።

የውጭ ኃይሎቹ ትርፍራፊ እርጥባን  ይረጫሉ። ባንዳው ህወሓትና አጋሮቹ ደግሞ ሀገራቸውን በሽርፍራፊ ዲናር ሽጠው የጥፋት መሣሪያ ሆነዋል። በመሆኑም ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን፣ ከሽፍትነትና ከመንደር  ሸቃጭነት በላይ ከፍ ሊል የማይችል የፖለቲካ ድንክዬ ነው። የሕዝብን ልብ ማግኘት ሲሳነው፣ በባዕዳን ትከሻ ላይ ተፈናጥጦ፣ ሌሎች ጽንፈኞችን አሰባስቦ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚቋምጥ የሥልጣን ጥመኛ ነው።

ነገር ግን፣  ኢትዮጵያ የትናንቷ አይደለችም። ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና የጸጥታ ኃይሎች  የትሮይ ፈረሱን ሆድ ካባ ገልጠው ሴራውን አደባባይ አውጥተውታል። የባንዳዎቹን አከርካሪ በመምታት አሽመድምደዋቸዋል። ዛሬ ይህ የጥፋት ኃይል በመጨረሻው ጣረ-ሞት ላይ ይገኛል፤ ትንፋሹ አጥሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚረጋገጠው በልጆቿ ፅናት እንጂ፣ ለባዕዳን ደጅ በመጥናት አይደለም። በዘመናት ታሪኳ በርካታ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን አስተናግዳለች። ሆኖም የዓለም ታሪክ የማይክደው አንድ ጽኑ እውነት አለ። በኢትዮጵያ ላይ የተፈጠሩ የጥፋት ጥምረቶች በሙሉ፣ በእውነት አደባባይ ሲያሸንፉ ታይቶ አያውቅም።

ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን፣ "ሀገርን ለማፍረስ ሞክሮ የከሸፈበት" ርካሽ የባንዳዎች ስብስብ ሆኖ በታሪክ መዝገብ ይጣላል። የጠላቶቿ ሴራ ይከሽፋል፤ ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ አንድነት ደምቃና ፀንታ ለዘላለም ትኖራለች!

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: