ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የቤተሰብ ቀኑን ባከበረበት መድረክ ላይ የድርጅቱ ባለቤት እና ሊቀመንበር ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ባስተላለፉት መልእክት፣ ሚድሮክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት መሆኑን ገልጸው የዕድገት ግስጋሴው በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥሉት ዓመታት ድርጅቱ ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ለበርካታ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል፡፡
አክለውም፣ “ድርጅታችን የሀገርን የልማት አቅጣጫ በመከተል ከመንግሥት ጋር በቅርበት እና በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ ነው” ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ያጋጠሙትን እና ተደቅነውበት የነበሩ ፈተናዎችን በድርጅቱ በተደረገው የአመራር ለውጥ አማካኝነት ማለፍ መቻሉን የጠቆሙት ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ፣ በአሁኑ ወቅት ሚድሮክ ወደ ተሻለ እና የላቀ የስኬት ጎዳና እየገሠገሠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የዕድገት ደረጃ በላይ እንድትራመድ በጋራ እና በትብብር መሥራት እንዳለበት የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ የሀገር አንድነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማሳሰብ “አንድ ላይ ሆነን የኢትዮጵያን ውድቀት የሚፈልጉ ጠላቶቻችን እንመክታለን” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ በሥራቸው የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ እና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የድርጅቱ ሠራተኞች እና አመራሮች ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት እና ዕውቅና ተበርክቶላቸዋል፡፡
በወይንሸት ደጀኔ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: