የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የክልሉን የ2019 የበጋ መስኖ ልማት ንቅናቄ መርሐ ግብር ዛሬ አስጀምረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በክረምት እና በበጋ ወራት በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩንም አብራርተዋል፡፡
በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በበጋ መስኖ ለመሸፈን መታቀዱን የጠቆሙት አቶ አሻድሊ፣ ለዕቅዱ ስኬታማነት የዘርፉ አመራሮች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ በበኩላቸው፣ በዘንድሮው የመስኖ ልማት አርሶ አደሮች በንቃት በመሳተፍ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የንቅናቄ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
ለዚሁ ሥራ 13 አዳዲስ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ የግንባታ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ተመልካቷል፡፡
በጀማል አህመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: