Search

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር፣ የዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ዕድገት እና የቀጠናዊ ትስስር ምሰሶ፦ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል

ሓሙስ መስከረም 07, 2019 40

በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረቅ ወደብ ገበያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የሚገኝ ዘርፍ ሲሆን፣ በቅርብ የገበያ ጥናቶች መሠረት በአውሮፓውያኑ 2026 የነበረው 1.09 ቢሊዮን ዶላር የገበያ መጠን 2035 ወደ 1.64 ቢሊዮን ዶላር ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ይህ ዓለም አቀፋዊ የገበያ ዕድገት የሚያሳየው፣ የባሕር ወደቦችን መጨናነቅ ለመቀነስ፣ የጉምሩክ አሰራርን ለማፋጠን እና የየብስ ሀገራትን ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ጋር በጥብቅ ለማስተሳሰር የደረቅ ወደቦች ሚና ወሳኝ እየሆነ መምጣቱን ነው።

 

የደረቅ ወደቦች በዋናነት በየብስ መንገድ፣ በባቡር መስመር ወይም እነዚህን ሁሉ በማቀናጀት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፤ የዕቃ መጫንና ማውረድ፣ ጊዜያዊ ማከማቸት እና የሽግግር ጭነት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ይሰጣሉ።

 

ኢትዮጵያም ይህንን ዓለም አቀፋዊ የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ እና አሰራር በመከተል የሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከልን በማስፋፋትና በማዘመን ረገድ አዲስ አገራዊና አህጉራዊ ምዕራፍ ከፍታለች።

60 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል የመጀመሪያ ምዕራፍ ማስፋፊያ በይፋ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ፣ የመደመር መንግሥት በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ለመሆኑና ለተግባራዊነቱ ትልቅ ማሳያ ነው።

የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ ለዓመታት የወደብ አገልግሎት እና የትራንዚት መጨናነቅ፣ ከፍተኛ የመጋዘን ወጪ እንዲሁም የተንዛዛ የጉምሩክ አሰራር በኢኮኖሚዋ ላይ ትልቅ ማነቆ ፈጥሮባት ቆይቷል።

ቀደም ሲል በግብርናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚመረቱ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዳይቀርቡ በቂና ዘመናዊ የሎጂስቲክስ አቅርቦት አለመኖሩ ትልቅ እንቅፋት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

በተለይም እንደ አቮካዶ እና ሙዝ ያሉ በቀላሉ የሚበላሹ የግብርና ምርቶችን ጥራታቸውን ጠብቆ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችሉ የቀዝቃዛ ኮንቴይነሮች አቅርቦት እና ዘመናዊ የማከማቻ መጋዘኖች መገንባታቸው የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነት አዲስ ደረጃ ላይ ያሸጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በማዕከሉ ምረቃ ወቅት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ያለው ሀገር ለማደግ ሎጂስቲክስ ከፍተኛ ጉልበት አለው።

የሎጂስቲክስ አገልግሎት ችግር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አንቆ የቆየ መሆኑን በማንሳት፣ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ እነዚህን ችግሮች እንደሚፈታ አስገንዝበዋል።

ይህ አገራዊ ስኬት ኢትዮጵያ 2018 . ካስመዘገበችው 10.2 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ ለቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገትም አስተማማኝ መሠረት ይጥላል።

ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከሉ በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ጣቢያዎችና ዘመናዊ መጋዘኖች ያሉት ሲሆን፣ ይህም የማዕከሉን የኮንቴይነር የመያዝ አቅም 500 ሺህ ወደ 1 ሚሊዮን በማሳደግ በእጥፍ አሳድጎታል።

የደረቅ ብትን ጭነቶችን በሀገር ውስጥ ማሸግ ማስቻሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠቡ ባለፈ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

የማዕከሉን የአሰራር ፍጥነት ለማሳደግ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው የባቡር ላይ ክሬን ከባቡር መስመር የሚደረገውን የኮንቴይነር ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት ያከናወናል። ሙሉ አሰራሩ በዘመናዊ ዲጂታል መሠረተ ልማት የተሳሰረ በመሆኑ ለተገልጋዮች ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎት ይሰጣል።

ይህ ማዕከል ከኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ዩጋንዳን የሚያስተሳስረው ደሱ ኮሪደር አካል በመሆኑ ሀገራችን በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃ ላይ ያላትን ስፍራ የሚያሻሽልና የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው።

ከማክሮ-ኢኮኖሚ አንጻር ሲታይ፣ የዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ ባደረጉት 200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ተጨማሪ 110 ሚሊዮን ዶላር ማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ አሰራር በከፍተኛ ሁኔታ ዘምኗል።

በዚህም ምክንያት ኮንቴይነሮች በወደብ የሚቆዩበት አማካይ ጊዜ 60 ቀናት ወደ 15 ቀናት ዝቅ ብሏል። ይህ የጊዜ ቅናሽ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለውጭ ወደቦችና ትራንዚት የምታወጣውን 2 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ከመቀነሱም በላይ፣ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት እንዳመላከተው በሎጂስቲክስ እጥረት ምክንያት በየዓመቱ በኢትዮጵያ ጠቅላላ ሀገር በቀል ምርት (GDP) ላይ ይደርስ የነበረውን 19 ቢሊዮን እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ አቅም ማጣት/ኪሳራ በከፍተኛ ሁኔታ ይታደጋል።

በዓለም አቀፍ እና በአህጉራዊ ደረጃ የዓለም ባንክ ባወጣው ጥናት እንደገለጸው፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ለአፍሪካ ቀጠናዊ ትስስር ተግባራዊ አርአያና ሞዴል ነው።

በአሁኑ ወቅት 85 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ንግድ ከአህጉሩ ውጭ ባሉ ሀገራት የሚከናወን እና በዋናነት ጥሬ ዕቃ ሲሆን፣ በአንጻሩ 60 በመቶ በላይ የሚሆነው የአፍሪካ የውስጥ ንግድ የተመረቱና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ያካተተ ነው።

በመሆኑም የሞጆ ደረቅ ወደብ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ግቦችን በማገዝ፣ አፍሪካውያን እርስ በርሳቸው እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በስፋት እንዲነግዱ እና አህጉራዊ የአቅርቦት ሰንሰለት እንዲጠነክር ያደርጋል።

በተጨማሪም በዘመናዊ የሎጂስቲክስ አሰራር ውስጥ የሚፈለገውን አካባቢን የመጠበቅና የካርቦን ልቀትን የመቀነስ (Green Logistics) መርህ በመከተል፣ የባቡር ትራንስፖርት አጠቃቀምን በማስፋፋትና የትራንስፖርት ወጪን እስከ 30 በመቶ በመቀነስ የኢትዮጵያንና የአካባቢውን ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ በዘላቂነት ያፋጥናል።

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: