Search

"ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ኖሯል፤ ይኖራልም!"

ማክሰኞ ሐምሌ 14, 2018 110

ታሪክና ምስክርነት

"መልሕቅ አርማዬ፣ ቀይ ባሕር ቤቴ፤ ጀግንነት ውርሴ፣ የአያት የአባቴ፤ ቃል ኪዳኔን ላድስ፣ ዳግም ለእናት ሀገር፤ ተከብሮ በደሜ፣ ለኖረው ባሕር በር፤ ... "

ይህን የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሐቅ የሚያንጸባርቀውን መዝሙር የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ፒቲ ኦፊሰር ፍሬሰናይ ከበደ የተቀኘው በከንቱ አልነበረም።

የዜማው ግጥም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት፣ የሕልውናዋ መሠረት እና ደም ሥሯ የሆነውን፤ ስትናፍቀውም ለዘመናት የኖረችውን ቀይ ባሕርን የተመለከተ ጥልቅ ሥነ ልቦናዊ መግለጫ ነው።

የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ቁርኝት የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ትርክት ሳይሆን፣ ከጥንት ሥልጣኔ ጀምሮ በዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች፣ ተጓዦች እና ተመራማሪዎች በስፋት የተመዘገበ የማይፋቅ እውነት ነው።

ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በግሪካዊ መርከበኛ የተጻፈው "የኤርትራ ባሕር ፔሪፕለስ" የተሰኘው ጥንታዊ ሰነድ፣ አዱሊስ የገናናው የአክሱም ሥልጣኔ ዋነኛ ወደብ መሆኗን በግልጽ ያስቀምጣል።

6ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ግሪካዊው ነጋዴ እና መነኩሴ ኮስማስ ኢንዲኮፕሌውስቴስ "ክሪስቲያን ቶፖግራፊ" በተሰኘው መጽሐፉ፣ የአክሱም ነገሥታት በቀይ ባሕር ላይ ስለነበራቸው የባሕር ኃይል እና የንግድ የበላይነት በቦታው ተገኝቶ ዘግቧል።

በዘገባውም፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ዋነኛ ባለቤት እንደነበረች አረጋግጧል።

ታዋቂው ሮማዊ ጸሐፊ ፕሊኒ ኤልደር እና የባይዛንታይን ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ፕሮኮፒየስም፣ የኢትዮጵያ መርከቦች በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የነበራቸውን ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ተጽዕኖ ዘግበዋል።

በተጨማሪም የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የአፄ ካሌብ የባሕር ኃይል የነበረውን ግዙፍ አቅም አብራርተው ጽፈዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና / ስቱዋርት መንሮ-ሄይ ያሉ የዘመናችን ታሪክ ተመራማሪዎችም፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ በቀይ ባሕር በነበራት የበላይነት ላይ የተገነባ ስለመሆኑ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በርካታ ዓለም አቀፍ የታሪክ ጸሐፊያን እና መዛግብት ጭምር በተደጋጋሚ ያረጋገጡት ሐቅ፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ሥልጣኔ ዋነኛ ፈጣሪ፣ ጠባቂ እና ባለቤት መሆኗን ነው።

እናም የቀይ ባሕር ጉዳይ የፖለቲካ ቁማር ወይም የሴራ ማስፈጸሚያ ጊዜያዊ አጀንዳ ፈጽሞ አይደለም።

ይልቁንም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከኖረችበት፣ ከታነጸችበት እና ታላቅነቷን ካረጋገጠችበት የተፈጥሮ የባሕር በሯ ጋር ተመልሳ የመገናኘት የሕልውና ጥያቄ ነው።

"ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ኖሯል፤ ይኖራልም!" የሚለው የታላቁ የጦር መሪ የራስ አሉላ አባነጋ ታሪካዊ ንግግር፣ የሀገራችንን የማይፋቅ ታሪካዊ መብት የሚያስረግጥ፣ ትውልድ የማይዘነጋው ሐቅ ነው።

ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን "አትንኩት፣ አታንሱት" በሚል አፋኝ የፖለቲካ ትርክት ዓይናችንን ለመሸፈን ቢሞከርም፤ አሁን ላይ ግን ጥያቄው የሁላችንም የጋራ አጀንዳ ሆኗል።

ትውልዱ ታሪኩን መመርመር እና እውነትን መጋፈጥ ጀምሯል፤ ይህን ሕልም እውን የማድረግ አደራውንም ተረክቧል።

በዚህም፣ የዘመናት ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለሷ እውነት ጎህ ሲቀድ የሚፈነጥቅ የፀሐይ ብርሃን ሆኖ ብቅ ብሏል።

አዎ፣ ሀገራችን ከኖረችበት፣ ከታነጸችበት እና የልብ ትርታዋ ከሆነው የባሕሯ ጋር በድጋሚ መገናኘቷ የማይቀር ታሪካዊ ግዴታችን ሆኗል።

በታሪክ፣ በመልክዓ ምድር እና በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠው እውነት ፍሬ አፍርቶ፣ የኢትዮጵያ መርከብ በክብር ወደ ቤቷ ተመልሳ መልሕቋን ትጥላለች።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: