ኢትዮጵያ በየዘመናቱ እጅግ ፈታኝ የሆኑ የጥፋት ወጥመዶች ቢደገሱላትም፣ በማይበገረው ጀግና ሠራዊቷ ክንድ እና መስዋዕትነት አያሌ የድል ታሪኮችን እየፃፈች ሉዓላዊነቷን አስከብራ ኖራለች።
የሰነፍ በትር የማይሰብረው እና የጊዜ እንቅፋት የማይጥለው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ዘመኑን ከሀገር ህልውና ጋር አስተሳስሮ የሚኖር የኅብረት እና የወንድማማችነት ታላቅ ተቋም ነው።
ወታደርነት ሀገርን አስቀድሞ ቤተሰብን፣ ልጅን እና የትዳር አጋርን ትቶ መውጣት፤ እንዲሁም "ወጥቶ መቅረት አለ" ብሎ አምኖ ለሌሎች መኖር ሲባል ውድ ሕይወትን አሳልፎ መስጠት ነው።
እየወደቁ ሀገርን ማንሳት፣ እየሞቱም ኢትዮጵያን ማስቀጠል የሠራዊታችን የዕለት ተለት ኑሮ ነው።
ይህ የሕዝብ እና የሀገር ዋልታ የሆነ ሠራዊት፣ የጫማውን ክር ሳይፈታ በየተራራው ዋርድያ እያደረ፣ ወጣትነቱን ለሀገር ገብሮ የሚኖር የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።
በጥይት አረር እየተቃጠለ፣ በእቶን እሳት መሀል እያለፈ እና በፈንጂ የተከበበ መሬትን እየተሻገረ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደርጋል።
በውጊያ መሀል በሕይወት ያጣውን ጓዱን ሀዘን ውጦ፣ አካሉ የጎደለበትን ወንድሙን ደግፎ "ቅድሚያ ለሀገር" በሚል ጽኑ የሀገር ፍቅር ወደፊት በመገስገስ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ያስከብራል። ኃያል ክንዱን በጠላት ላይ እያሳረፈ ሀገርን ከፈተና፣ ወገንን ከመከራ ይታደጋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጠላትን የሚያርበደብድ የኃይል ክንድ ብቻ ሳይሆን፣ ሰው መሆንን ብቻ ሚዛኑ ያደረገ የሩህሩህነት ተምሳሌትም ነው።
ለተራበው ካለው እያካፈለ፣ ለተጠማው እያጠጣ እንዲሁም ለማረከው ጠላት ሳይቀር የሚራራ እውነተኛ የሕዝብ አለኝታ ነው።
በሰላሙ ጊዜም ቢሆን በተሰማራበት ግዳጅ ሁሉ ከሕዝቡ ጎን በመሰለፍ በልማት ሥራዎች ላይ አሻራውን ያኖራል።
በዱር በገደሉ፣ በበረሃው ግለት እየነደደ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለወገኑ ደህንነት የማይተካ ሕይወቱንና አካሉን ለሚሰጠው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሁሉ የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባዋል።
በመቅደላዊት ደረጀ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: