Search

የአፍሪካን የጤና ሥርዓት በራሳችን የፋይናንስ ዐቅም የምንገነባበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ረቡዕ ሐምሌ 15, 2018 40

የአፍሪካን የጤና ሥርዓት በራሳችን የፋይናንስ ዐቅም የምንገነባበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በጋና አክራ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ ልዩ የመሪዎች የጤና ጉባኤ ላይ ተገኝተን የኢትዮጵያን ተሞክሮና ለቀጣይ የአህጉራችን የጤና አቅጣጫ ያለንን ቁርጠኝነት አጋርተናል ብለዋል።

የውጭ ርዳታ እየቀነሰ መምጣቱ ለአህጉራችን ትልቅ ፈተና ቢሆንም፤ በራሳችን ዐቅም ላይ የተመሠረተ፣ የጸና እና ዘላቂ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ግን ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሮልናል ነው ያሉት።

ጉባኤው እ.ኤ.አ. በ2030 ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን፣ ቲቢንና ወባን ከኅብረተሰብ ጤና ሥጋትነት የምናስወግድበትን፣ መከላከል የሚቻል የእናቶችና ሕፃናት ሞትን የምንገታበትን እና ዘላቂ የፋይናንስ ዐቅማችንን የምናጠናክርበትን አህጉራዊ ፍኖተ ካርታ የምንቀርጽበት የታሪክ ምዕራፍ ነው ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ራስን የመቻል ሀገራዊ ርዕይን መሠረት በማድረግ በጤናው ዘርፍ ያሳካችውን ተሞክሮዎች በመድረኩ ለጉባኤው መካፈሏንም ገልጸዋል።

አፍሪካ በራሷ ዐቅም የሚመራ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል በቂ ዕውቀት፣ ተቋማትና ተሞክሮ እንዳሏት የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጤናው መስክም አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገን የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ወደ ተጨባጭ ተግባር መቀየር ብቻ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል እንዲሁም ከአባል ሀገራት ጋር በመተባበር ጤናማና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: