Search

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት

ረቡዕ ሐምሌ 15, 2018 41

የአፍሪካን የጤና ሥርዓት በራሳችን የፋይናንስ ዐቅም የምንገነባበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን!

በጋና አክራ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ ልዩ የመሪዎች የጤና ጉባኤ ላይ ተገኝተን የኢትዮጵያን ተሞክሮና ለቀጣይ የአህጉራችን የጤና አቅጣጫ ያለንን ቁርጠኝነት አጋርተናል።

የውጭ ርዳታ እየቀነሰ መምጣቱ ለአህጉራችን ትልቅ ፈተና ቢሆንም፤ በራሳችን ዐቅም ላይ የተመሠረተ፣ የጸና እና ዘላቂ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ግን ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሮልናል።

ጉባኤውም እ.ኤ.አ. በ2030 ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን፣ ቲቢንና ወባን ከኅብረተሰብ ጤና ሥጋትነት የምናስወግድበትን፤ መከላከል የሚቻል የእናቶችና ሕፃናት ሞትን የምንገታበትን እና ዘላቂ የፋይናንስ ዐቅማችንን የምናጠናክርበትን አህጉራዊ ፍኖተ ካርታ የምንቀርጽበት የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ኢትዮጵያ ራስን የመቻል ሀገራዊ ርዕይን መሠረት በማድረግ በጤናው ዘርፍ ያሳካቻቸውን ተሞክሮዎች በመድረኩ ለጉባኤው አካፍላለች።

አፍሪካ በራሷ ዐቅም የሚመራ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል በቂ ዕውቀት፣ ተቋማትና ተሞክሮ አሏት! በጤናው መስክም አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገን የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ወደ ተጨባጭ ተግባር መቀየር ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል እንዲሁም ከአባል ሀገራት ጋር በመተባበር ጤናማና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: