Search

ዓለም አቀፉን የውኃ ሕግ መርህ ያከበረ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

ረቡዕ ሐምሌ 15, 2018 51

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተመርቆ የተሟላ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ላይ ከደረሰ እነሆ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።

ይህ ታሪካዊ ክስተት ከውኃ መሐንዲስነት ስኬት ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ እና በናይል ተፋሰስ ለዘመናት የነበረውን ጂኦ-ፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ የቀየረና መዋቅራዊ ሽግግር ያመጣ እውነታ ነው።

በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ መርሆዎች ላይ የተመሠረተው ይህ የልማት እርምጃ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በገዛ የተፈጥሮ ሃብታቸው ላይ የልማት ውሳኔ ለማሳለፍ የማንም ሀገር ይሁንታ እንደማያስፈልጋቸው በተግባር ያረጋገጠበት የአዲሱ ዘመን ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ስታከናውን ዲፕሎማሲውን እያጎለበተች እንጂ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነትን እየረበሸች አለመሆኑን የዓለም አቀፍ ሕግጋትና የቀጣናው የማክሮ-ኢኮኖሚ ትስስር እውነታዎች በግልፅ ይመሰክራሉ።

በዚህ የሕግና የዲፕሎማሲ አውድ የዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ማዕቀፍ እና የፍትሐዊነት መርህ ማዕከላዊ ስፍራ ይይዛሉ።

በፈረንጆቹ 1997 የፀደቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች  አጠቃቀም ስምምነት እንደ ዓለም አቀፍ የልማድ ሕግ (Customary International Law) የሚያገለግል ሲሆን፣ "ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም" የሚለውን ዓላማ  ያነገበ ነው።

በዚህ ህግ አንቀፅ 5 ላይ የሰፈረው መርህ የሚያስቀምጠው ማንኛውም የተፋሰስ ሀገር በግዛቱ ውስጥ በሚያልፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ ያለውን የውኃ ሀብት የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳለውና አጠቃቀሙም የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦግራፊያዊ ፍላጎቶችን ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ነው።

የዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት (ICJ) ሳይቀር "ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም" የበላይ መርህ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ልማት በድርድርና በማካካሻ መመራት እንጂ ሙሉ በሙሉ ሊቆም እንደማይችል የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል።

ዓለም አቀፍ ህግ ይህ ሆኖ ሳለ፣ የዓባይ ውኃን ከ85 በመቶ በላይ የምታመነጨውን ኢትዮጵያ ማግለልና ማዳከም የግብፅ የዘመናት መዋቅራዊ የጂኦ-ፖለቲካ ሴራ ሆኖ ቆይቷል። ይህ የጂኦ-ፖለቲካ ስሌት ከጥንት ጀምሮ የዓባይን ምንጭ የመቆጣጠር ወይም ምንጩ ያለበትን ሀገር ደካማ አድርጎ የማቆየት ቋሚ ፖሊሲ ነው።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን “ታላቋን ግብፅ” ለመመሥረት የተደረጉት የጉንደትና ጉራዕ ውጊያዎች በኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት የመከኑት የወረራ ሙከራዎች የዚህ ታሪካዊ ማሳያ ናቸው። በ1959ኙ ስምምነትም ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ተገልላ ምንም ድርሻ ሳይኖራት  የውኃ አስተዋፅኦ የሌላት ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር፣ ሱዳን ደግሞ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መውሰዳቸው የግብፅን የውኃ ባለቤትነት የበላይነት አቋም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ጠንካራና በኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያ ይህንን የተፈጥሮ መብቷን ማስከበሯ ስለማይቀር ከገማል አብዱል ናስር ኢትዮጵያን የመክበብ ፖሊሲ እስከ አንዋር ሳዳት ወታደራዊ ዛቻ፣ ከሁስኒ ሙባረክ የብድር ማዕቀብ ዘመቻ እስከ አብዱልፈታህ አልሲሲ ቀጣናዊ ወታደራዊ ስምምነቶች ድረስ ኢትዮጵያን የማግለል ፖሊሲ እስከዛሬ አልተቀየረም፡፡

ሆኖም የግድቡ ግንባታና ስኬት ይህንን የግብጽን የዘመናት ሴራ በተግባር በማፍረስ የሃይድሮ-ፖለቲካዊ በላይነት እንዲያበቃለት አድርጓል። ጉዳዩንም ከአንድ ወገን የበላይነት ወደ የጋራ ሀብት አስተዳደር በማሸጋገር፣ በግብጽ ሚዲያዎች ሲቀነቀን የነበረውን የ"ውኃ ጦርነት" ትርክት አክሽፎታል።

እናም ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የአፍሪካ ቀንድ የማክሮ-ኢኮኖሚ ትስስር አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን መገንዘብ ያሻል። የሕዳሴው ግድብ የሚያመነጨው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ በቀጣናው ከሚገነቡ አዳዲስ የትራንስፖርት ኮሪደሮችና የተስፋፉ አማራጭ የባሕር ወደብ መሠረተ-ልማቶች ጋር ሲጣመር ወጪን ይቀንሳል።

ይህ ውህደት ድንበር ዘለል የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ዕውን በማድረግ፣ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን በማሳደግና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን በተግባር በመደገፍ ጠንካራ ቀጣናዊ የንግድ ማዕቀፍ ይፈጥራል።

በዚህም ኃይልን እንደ ቀጣናው "የደም ዝውውር ሥርዓት"፣ የትራንስፖርት ኮሪደሮችን ደግሞ እንደ "ደም ስሮች" በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ የራሷን የመልማት መብት ከማረጋገጥ አልፋ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በተግባር እያሸጋገረች ትገኛለች።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: