የፖለቲካ ድርጅቶች ከአላማቸዉ ሲፋቱ የሚኖራቸዉ ዕድል ከታሪክ መድረክ በክብር መሰናበት ሳይሆን ወደ ለየለት የውንብድና፣ የቅጥረኝነትና የጥፋት ማዕከልነት መቀየር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቆሞ ቀሩ የህወሐት ቡድን የውድቀት ጉዞ በተግባር የተረጋገጠ የታሪክ እውነት ነው።
በአንድ ወቅት ሀገራዊ የፖለቲካ ማዕከልን ተቆጣጥሮ የነበረው ይህ ቡድን፣ ዛሬ ላይ የፖለቲካ ፓርቲነትን ካባ አውልቆ ጥሎ፣ የጥቂት ግለሰቦችና የቤተሰብ ጥቅም ማስከበሪያ ወደሆነ "የሰፈር ስብስብና" የወንበዴዎች ጥርቅምነት ወርዷል።
ይህ አይነቱ ተቋማዊ መበስበስ በፖለቲካ ፍልስፍና እና የታሪክ ሳይንስ አስተምህሮዎች ውስጥ ድንገት የሚፈጠር ውጫዊ አጋጣሚ ሳይሆን ከውስጣዊ የራዕይ መክሸፍና ከህዝባዊ ቅቡልነት ማጣት የሚጀምር የተፈጥሮ ህግ ነው።
ጀርመናዊው የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ ሮበርት ሚሼልስ እ.ኤ.አ. በ1911 "የኦሊጋርኪ መደበኛ ህግ" (Iron Law of Oligarchy) በሚል ባስቀመጠው ጽንሰ ሃሳብ ከምግባሩ የተፋታ ማንኛውም ህዝባዊ ነኝ ባይ ድርጅት በሂደት ውስጥ ስልጣንን አከማችቶ የራሱንና የቅርብ ስብስቦቹን ጥቅም ብቻ ወደሚያስከብርበት የጥቂቶች የበላይነት (Oligarchy) መለወጡ አይቀሬ መሆኑን ያስረዳል። የህገወጡ ህወሐት የአሁኑ ቁመናም የዚሁ ፍልስፍና ህያው ማሳያ ሆኖ ነዉ።
ድርጅቱ ለህዝብ የቆመ መስሎ የሚታይበትን የውሸት ጭምብል ሙሉ በሙሉ ተገፍፎ ከታየ የሰነበተ ሲሆን ድርጊቱም ከፖለቲካዊ ውድቀት አልፎ በሀገር ክህደት የተሞላ ነው።
ሁልጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት ወደኋላ ብሎ የማያውቀው ይህ የባንዳ ስብስብ፣ ሀገራችንን የባህር በር በማሳጣት ታሪካዊ ስህተት የፈጸመ ከመሆኑም በላይ፣ በሰሜኑ የድንበር ጦርነት ወቅትም የሀገራችንን ሉዓላዊነት አሳልፎ በመስጠት የከፋ ወንጀል ፈጽሟል።
ከዚህም ባሻገር የትግራይ ወጣቶችን በውሸት ትርክት ለጦርነት ከማሰለፉም በላይ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ለባዕዳን ሀገራት ለቅጥረኝነት አሳልፎ እስከመሸጥ የደረሰ የወረደና የዘቀጠ ስብስብ ነው።
የህዳሴው ዘመን ፖለቲካ ፈላስፋ ኒኮሎ ማኪያቬሊ እንደሚለው ህዝብን በብዝበዛና በፍርሃት ለማስገበር የሚሞክር ድርጅት ህዝባዊ መደገፊያውን ማጣቱ አይቀርም። ጆን ሎክ በበኩሉ የማስተዳደር ቅቡልነት የሚመነጨው ከህዝብ ፈቃድና ጥቅም ማስጠበቅ መሆኑን ቢሞግትም፣ የከሰረዉ የህወሐት ቡድን ግን የሥልጣን ህልውናውን ለማስጠበቅ ሲል የትግራይን ሕዝብና ወጣት ለከፋ ተስፋ መቁረጥ ዳርጎት ይገኛል።
ከፖለቲካዊ ዓላማ ርቆ ወደ ለየለት ማፊያዊ አደረጃጀት የተቀየረው ይህ የግብጥና ሻቢያ ተላላኪ ቡድን፣ ዛሬ ላይ ኑሮውን የመሰረተው በኮንትሮባንድ ንግድና በህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ወንጀል ላይ ነው። በተለይም በህገወጥ መንገድ የወርቅ ማዕድንን በማዘዋወርና በመዝረፍ የጥቂት የቤተሰብ መረቦችን ኪስ በማደለብ ላይ ተጠምዷል።
የጥንቱ ግሪክ ፈላስፋ አሪስቶትል በ"ፖለቲካ" መጽሐፉ ላይ እንዳስረዳው፣ አንድ ድርጅት አቅጣጫውን ስቶ የጥቂቶችን ጥቅም ብቻ ማሳደጃ ከሆነ ወደ አምባገነንነት ወይም ኦሊጋርኪ ይለወጣል። እንዲህ ያሉ ሥርዓቶች ደግሞ የራሳቸውን ውድቀት በራሳቸው ውስጣዊ መበስበስ የሚያፋጥኑ ሲሆን ህወሐትም ይህንን ውስጣዊ መበስበስ ለመሸፈን ሲል የኢትዮጵያን ሀገራዊ ጥቅም በሚቃወሙ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ኪስ ውስጥ ገብቶ ጉዳይ አስፈጻሚ (Proxy Agent) በመሆን ሀገር ለማተራመስ እየሰራ ይገኛል።
በፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ የሰፈነዉን ሰላም በማደፍረስና ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት ለማስገባት የሚያደርገው ጥረትም የዚሁ የተረጋገጠ የቅጥረኝነት ተግባሩ አካል ነው።
በፖለቲካ ፍልስፍና መነጽር ሲመዘን የህወሐት ውድቀት ገና ወደፊት የሚከሰት አጋጣሚ ሳይሆን ቀድሞ የተረጋገጠ የታሪክ እውነታ ነው።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሰፈርና የአንድ ቤተሰብ ጥቅም ማስከበሪያ እንዲሁም የተራ ኮንትሮባንዲስቶችና ቅጥረኞች ስብስብ ከሆነ በኋላ፣ በታሪክ ውስጥ እንደገና የማንሰራራት አቅሙ ሙሉ በሙሉ ይከስማል።
በመሆኑም ከዚህ ህገወጥ የወንጀለኛ ስብስብ ውድቀት በኋላ የሚመጣው ብቸኛው አማራጭ፣ የትግራይ ሕዝብ እውነተኛ ሰላሙን፣ ብሔራዊ አንድነቱንና ዲሞክራሲያዊ መብቱን የሚያረጋግጥበትን አዲስ ሀገራዊ ምዕራፍ መክፈት ብቻ ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: