የኢትዮጵያ የታሪክ ገጾች ሲገለጡ፣ የተስፋና የጥልቅ ስብራት፣ የመገንባት ሙከራና መልሶ የመፍረስ አዙሪቶች ሲፈራረቁባቸው ኖረዋል። ለበርካታ ዘመናት ኢትዮጵያውያን የለፉበትን ንብረት እያወደሙና ያረጀውን እያፈረሱ አዲስ በመገንባት አስከፊ አዙሪት ውስጥ መኖራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ይህ ዘርፈ ብዙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራት በአንድ ጀንበር የተፈጠረ ክስተት ሳይሆን፣ ከአንዱ ሥርዓት ወደ ሌላው ሲንከባለል፣ ሲወሳሰብና ሲደራረብ የመጣ ሥር የሰደደ ማነቆ ነበር።
በዘውዳዊው ሥርዓት ተጠንስሰው የነበሩትን ጅማሬዎች፣ የደርግ ሥርዓት በሶሻሊዝም ርዕዮት ሲያጠፋቸው ታይቷል። በተቃራኒው ደግሞ በደርግ የተጀመሩትን ኢህአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲሽራቸው ተመልክተናል፣ አንዱ ሊበራሊዝም ይበጀናል ሲል፣ ሌላው ሶሻሊዝም፣ ቀጣዩ ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እያለ ሲዋዥቅ፤ አንዱ ሥርዓት የገነባውን ሌላኛው እያፈረሰ፣ አንዱ የሰጠውን ሌላው እየነጠቀ ሀገራችንን ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ቋሚ እሴትና አሻራ እንዳይኖራት ተደርጎ ቆይቷል።
ይህ ኃላፊነት የጎደለው ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ቅብብሎሽ ያመጣው መዘዝ እጅግ ከባድ ነበር። አጠቃላይ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ስብራት አጋጥሞት፣ መንግሥታዊ ተቋማት የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ እንኳ መክፈል ወደማይችሉበት የድቀት አዘቅት ውስጥ ተዘፍቀው ነበር። በየአካባቢው በከፍተኛ በጀት የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በሙስና፣ በምዝበራና በአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት ቆመው ቀርተው የብክነት ሐውልት ሆነው ነበር።
የኢትዮጵያ የዕድገት ተስፋ እጅግ አሳሳቢና ጨለማ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ሀገራችን ከተደቀነባት ጫና የተነሳ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱ ከዐቅሟ በላይ ለሆነ ዕዳ ዳርጓት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዋጋ ንረት የዜጎችን ኑሮ አክብዶት ቆይቷል።
ይሁን እንጂ፣ ይህን የቁልቁለት ጉዞ በመግታትና ታሪካዊውን ስብራት በመጠገን፣ የለውጡ ኃይልና አዲሱ ትውልድ አለመቻልን የረታ ጀግንነት ፈፅሟል። ይህ የለውጥ ትውልድ ኢትዮጵያን ቀና ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ካለችበት አዘቅት እንድታንሰራራና አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ እንድትጀምር አድርጓል።
የተበላሹ አሠራሮችን በማረም፣ ኢኮኖሚው ከዕዳ ወደ ምንዳ እንዲሸጋገር በማድረግና ለዘመናት ቆመው የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ፈጠራ በታከለበት ፍጥነት በማጠናቀቅ ሀገራችንን ወደ ማይቀለበስ የዕድገት ምኅዋር አስገብቷታል።
ዛሬ ላይ በሁሉም መስኮች እየተመዘገቡ ያሉት ዓለምን ያስደመሙ ስኬቶች፣ የትውልዱን የማይበገር አርበኝነት በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው። ከግብርና እስከ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ ከመሠረተ ልማት እስከ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራና በቱሪዝም ልማት የተመዘገቡት እመርታዎች ኢትዮጵያ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና በፍጥነት እየገሰገሰች መሆኗን ያሳያሉ።
በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲው መስክም፣ ሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነትና ተቀባይነት ዳግም አብቧል። ጠንካራ የተቋማት ሪፎርም እና የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ለዘላቂ ሀገረ መንግሥት ግንባታው ጽኑ መሠረት ጥለዋል።
በአጠቃላይ፣ ይህ አለመቻልን ያሸነፈ የትውልድ ጉዞ፣ የትናንትናውን ምስቅልቅል ታሪክ ቀይሮ ብሩህ ተስፋን አጭቋል። የታሪክ እስራትን በጥበብ በጣጥሶ፣ ስብራትን ወደ ዕድገት ለውጦ፣ እምቅ አቅም አውጥቷል። የተከማቹ ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር፣ ዛሬ ላይ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች ጠንካራ ኢትዮጵያ፣ ጠንካራ ሀገር እና መንግሥት ግንባታ አስተማማኝ መሰረት እየተጣለ ይገኛል። አለመቻልን በረታው በዚህ የትውልድ አርበኝነት፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ልዕልና ከምንጊዜውም በላይ በደማቁ ተረጋግጧል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: