Search

የምድራችን ሳንባ በመጨረሻም እፎይ አለ! አስደሳች ዜና ከአማዞን ደን

ረቡዕ ሐምሌ 15, 2018 83

ተፈጥሮ ራሷን እያዳነች ይሆን? 60 በመቶ ያህል የብራዚልን ክፍል የሚሸፍነውና የዓለማችን ትልቁ የአማዞን ደን፣ በአውሮፓውያኑ 2025 አስደሳች ሪከርድ አስመዝግቧል።

ማፕ ባዮ ማስ (MapBiomas) የተሰኘው ታማኝ የደን ጭፍጨፋ ተቆጣጣሪ ተቋም እንዳስታወቀው፣ ዘንድሮ በብራዚል አማዞን ደን ውስጥ በእሳት የተጎዳው መሬት 3.1 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው።

አስቡት... ይህ አሃዝ ካለፈው ዓመት አስደንጋጭ የ15.8 ሚሊዮን ሄክታር ውድመት ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም ግዙፍ መሻሻል የታየበት ነው።

ይህ ብቻ አይደለም የዘንድሮው አስደሳች አሃዝ ቡድኑ ባለፉት 30 ዓመታት የሳተላይት መረጃዎችን መሰብሰብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲታይ፣ እጅግ ዝቅተኛው የደን ቃጠሎ መጠን ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

ይህም ለዓለማችን የአየር ንብረት ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ክስተት መሆኑ አያጠራጥርም። ሆኖም ግን የተፈጥሮ ነገር አይታወቅምና ሙሉ በሙሉ ዘና የምንልበት ጊዜ አሁን አይደለም።

ለዚህ አዎንታዊ ለውጥ የላ ኒና (La Niña) ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን፣ ሆኖም የኤል ኒኖ (El Niño) የአየር ፀባይ ደረቁን ወቅት ሊያራዝመው ስለሚችል የቃጠሎ አደጋው በድጋሚ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

አሁንም ቢሆን የዓለማችንን ሳንባ ከጥፋት መጠበቅና የተፈጥሮን ሚዛን ማስጠበቅ የሁላችንም ትልቁ የቤት ሥራ ሆኖ ይቀጥላል።

ይህ አስደሳች ውጤት ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ አማዞንን ለመጠበቅ የገቡትን ቃል የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ በመጪው ጥቅምት ወር ለሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ ትልቅ ጉልበት እንደሚሆናቸው ተገልጿል።

ምንም እንኳን አሃዙ እጅግ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ ይህን እንደ ዘላቂ የመሻሻል አዝማሚያ አድርጎ በመደምደም የቅድመ መከላከል ሥራዎችን ማዘግየት እንደማይገባ ተመራማሪዎች አሳስበዋል።

በሲሳይ መንግስቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: