Search

በወታደራዊ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የታጠቀው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፤ የሉዓላዊነትና የሰላም አስተማማኝ ዋስትና

ረቡዕ ሐምሌ 15, 2018 129

የአንድ ሀገር ብሔራዊ ክብር፣ ሰላምና ልማት አስተማማኝ የሚሆነው ሉዓላዊነቷን ሊያስከብር የሚችል ጠንካራ እና ዘመናዊ የጥበቃ ተቋም ሲገነባ ነው።

በዚህም 90 ዓመታትን የሚጠጋ አንጸባራቂ ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸው ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራዎች እና የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከማስከበር አንጻር ያከናወናቸው ገድሎች ተቋሙን በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ካሉ ግንባር ቀደም የአየር ኃይል ተቋማት ተርታ አሰልፈውታል።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ የተካሄደው የሪፎርም ሥራ የተቋሙን አስተሳሰብ፣ የሰው ኃይል አቅም እና የቴክኖሎጂ ደረጃ የቀየረ ስር ነቀል ሽግግር ነው። የሪፎርሙ ቀዳሚ ትኩረት የአየር ኃይሉን አባላት በትምህርት፣ በሥነ-ልቦና እና በወታደራዊ ሳይንስ ማብቃት የነበረ ሲሆን፣ የአየር ኃይል አካዳሚ በዘመናዊ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች እና ስልጠናዎች እንዲደራጅ ተደርጓል።

ይህም ተቋሙ በማንኛውም የአየር ሁኔታ እና ተልዕኮ ውስጥ በላቀ ብቃት መዋጋት የሚችሉ ፓይለቶችን፣ የቴክኒክ ባለሙያዎችን እና የስትራቴጂ አዋቂዎችን በራስ አቅም እንዲያፈራ አስችሎታል። በዚህም ከፖለቲካዊ እና ወገንተኝነት አስተሳሰብ የጸዳ፣ ለሕገ-መንግሥቱ እና ለሀገር ሉዓላዊነት ብቻ የሚገዛ ፕሮፌሽናል ኃይል መገንባት ተችሏል።

አየር ኃይሉ ዘመኑ ከደረሰበት የጦርነት ሳይንስ ጋር እራሱን ለማስማማት ባለፉት ዓመታት ዘመናዊ የሰው አልባ አውሮፕላኖችን በስፋት በመታጠቅ የክትትልና የቅድመ መከላከል አቅሙን አሳድጓል።

የነባር ተዋጊ ጄቶችን እና የትራንስፖርት ሄሊኮፕተሮችን አቅም ለማሳደግ በከፍተኛ ደረጃ የጥገና ሥራዎችን በሀገር ውስጥ መሐንዲሶች ማከናወን የቻለ ሲሆን፣ የራዳር እና የደኅንነት መቆጣጠሪያ ሲስተሞችንም ወደ ዲጂታል ሥርዓት በመቀየር የአየር ክልል ጥበቃውን ይበልጥ አስተማማኝ አድርጓል።

በሪፎርም ሥራዎቹ የሀገርን ደኅንነትና ሉዓላዊነት በፅኑ መሠረት ላይ መገንባት ዋነኛ ግብ ያደረገው ተቋሙ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ካጋጠሟት ውስጣዊና ውጫዊ የደኅንነት ስጋቶች አንጻር የወሰዷቸው እርምጃዎች ታሪካዊ መሆናቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላምና የኅልውና ስጋት ውስጥ በነበረችበት ወቅት፣ አየር ኃይሉ የሰማይ ላይ የበላይነትን በመያዝ የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ስትራቴጂያዊ ይዞታዎች በማውደም እና የሎጂስቲክስ መስመሮቻቸውን በመቁረጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በጦርነቱ ወቅት የወሰዳቸው ጥቃቶች በንጹሐን ዜጎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ የጠላትን አቅም በማዳከም ረገድ ውጤታማነቱን ያሳዩ ነበሩ።

የኢትዮጵያን የአየር ክልል ያለፈቃድ ለመጣስ የሞከሩ ውጫዊ ትንኮሳዎችን በመቀልበስ ረገድ አየር ኃይሉ በተጠንቀቅ በመቆም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ተወጥቷል።

ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን፣ የኮንትሮባንድ ንግድን እና የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴ ከሰማይ ላይ በመቆጣጠር ረገድ የድንበር ጠባቂ መከታ ሆኖ አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል።

የኢትዮጵያ የልማት እና የሉዓላዊነት ማሳያ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተለያዩ የአየር ላይ ስጋቶች ለመጠበቅም አየር ኃይሉ ዘመናዊ የጸረ-አውሮፕላን መከላከያዎችንና የራዳር ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም 24/7 አስተማማኝ ከልል በመፍጠር ታሪካዊ አደራውን እየተወጣ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተከናወኑት የሪፎርም ሥራዎች ተቋሙን የታሪክ አኩሪ ቅርስ ብቻ ሳይሆን፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት እና የነገዋ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና አድርገውታል።

አየር ኃይሉ ዛሬ ላይ የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የሚያስችል ትልቅ አቅም መገንባቱን በተግባር አሳይቷል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሪፎርም “የአየር ኃይላችን የኢትዮጵያ ኩራት” የሚለውን መፈክር በተግባር የገለጸ እና የሀገርን ሉዓላዊነት በፅኑ ዓለት ላይ ያቆመ ስኬታማ ምዕራፍ ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: