ከዚህ ቀደም በትጥቅ ትግል ጎዳና ቆይቶ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል የተቀላቀሉት አቶ ማስረሻ ሰጤ፣ አሁን ላይ በመዲናችን አዲስ አበባ እየተካሄደ ስላለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተስፋቸውን አጋርተዋል።
አቶ ማስረሻ እንደገለጹት፣ ሀገራዊ ምክክሩ የሕዝብ ጥያቄዎች በውይይትና በድርድር እንዲፈቱ ምቹ መድረክ የፈጠረ አሳታፊ እና በርካታ ሐሳቦች የሚነሱበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
ይህ ሂደት ኢትዮጵያን ለዓመታት ወደ ግጭት ውስጥ የከተቱ ዘላቂ ጥያቄዎች እውነተኛ ምላሽ ያገኛሉ የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳለቸውም ተናግረዋል።
“የሐሳብ ብዝሃነት ውበት እንጂ ችግር አይደለም” የሚሉት አቶ ማስረሻ፣ ቀደም ሲል የነበረው ቁርሾ የተፈጠረው ያንን ብዝሃነት ከምንጠቀምበት መንገድ ጉድለት መሆኑን ጠቁሞ፣ አሁን የተዘጋጀው መድረክ ግን ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተወጣጡ በመሆኑ የበላይነት ወይም የበታችነት ስሜት ሳይኖር የተሻለው ሐሳብ አሸንፎ የሚወጣበትና አገርን በጋራ ወደፊት የሚያራምድ ውጤት እንደሚመጣበት አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም ለነበሩት ጥያቄዎች መነሻ የሆኑትን ታሪካዊ ስህተቶች፣ የመንግሥት አወቃቀር፣ ሕገ-መንግሥታዊ እና ሌሎች ጣልቃገብነቶችን እንዲሁም አገርን ለመከፋፈል የሚደረጉ እውነትነት የሌላቸውን ነገሮች በብስለት አይቶ ለማስተካከል ሂደቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጿል።
ይህም ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ለልጆቻችን እና ለእህት ወንድሞቻችን የተሻለችና በጋራ የምንኖርባት አገርን ለማስረከብ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
የተሻለች አገርን የመገንባት ውጤት የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የሁሉም ድርሻ መሆኑን ያነሱት አቶ ማስረሻ፣ ሕዝቡ እና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ አካላት ሐሳባቸውን በንቃት በማንጸባረቅ ኢትዮጵያን በጋራ የሚገነቡበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ራሳቸው ከመጡበት አካባቢ አንጻር የነበሩትን ጥያቄዎች ለማስመለስ የተሄደበት መንገድ ስህተት መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል።
በመሣሪያ እና በግጭት የሚደረግ ጉዞ አገርን ወደፊት እንደማያራምድና የሆነን ቡድን ሥልጣን ላይ ከማውጣት ባለፈ ያ አካል ደግሞ ጨቋኝ ላለመሆኑ ምንም ዋስትና እንደሌለው አስታውሰዋል።
በመሣሪያ እና በግጭት ሳይሆን በመነጋገር፣ በመግባባት እና በመመካከር ሁላችንም በጋራ የተሻለችውን አገር መፍጠር እንችላለን በማለት ገልጸዋል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: