“ውሃ የቀጣዩ ክፍለ ዘመን ነዳጅ ነው” የተባለው ትንቢት በተግባር የሚታየው በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ሲሆን፣ የዛሬው ትውልድም ይህንን ያለፈውን ዘመን ቁጭት በሚገባ ተረድቶ የጠላቶቹን የሴራ ድር በአሸናፊነት በመበጠስ ላይ ይገኛል።
በፈረንጆቹ 1800ዎቹ መጀመሪያ ግብጽን ያስተዳድሩ የነበሩት ቱርካውያን ፈረንሳውያንን አማካሪ በማድረግ፣ በዓባይ ወንዝ ዳርቻ የጥጥ እርሻን በማስፋፋት አውሮፓን በጥጥ ምርት መቆጣጠር ችለው ነበር። ይህ የኢኮኖሚ ጥማት ግብጽ የዓባይን ተፋሰስ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንድትነሳሳ አደረጋት።
ግብጽ "ከምንጩ እስከ አፍ" የሚለውን የቅዠት ፖሊሲ አንግባ በ1820ዎቹ የሱዳንን ሰሜናዊ ክፍል ከወረረች በኋላ፣ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር ምፅዋን፣ ከረንን እና ሀረርን ጭምር ለመቆጣጠር ሞክራለች። ነገር ግን በጉንደትና በጉራዕ ጦርነቶች ጀግናው አሉላ አባነጋ የግብጽን ጦር ዶግ አመድ በማድረግ አሳፋሪ ሽንፈት አከናንቧቸዋል። በሽንፈቷ ምክንያት ኢኮኖሚዋ ክፉኛ የተናጋባት ግብጽ፣ የስዊዝ ካናል ድርሻዋን ለመሸጥ ብትገደድም ቀውሱን ማምለጥ አልቻለችም።
የፋሾዳው ፍጥጫና የተጠላለፈው የቀኝ ገዥዎች ሴራ
ከዚህ ቀውስ በኋላ፣ እንግሊዝ የቀይ ባሕርን እና ዓባይን ለመቆጣጠር ግብጽን በቦምብ ደብድባ በቅኝ ግዛት ስር አዋለች። የእንግሊዝ ዋነኛ ፍላጎት ለማንቸስተር የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ የጥጥ አቅርቦት ማግኘት ነበር። ይህንንም ለማሳካት ሱዳን ውስጥ 'ፋሾዳ' በተባለ ስፍራ ዓባይን ለመቆጣጠር ከምትገሰግሰው ፈረንሳይ ጋር በፈረንጆቹ 1898 ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ገብታ ነበር። ፈረንሳይ ከምዕራብ አፍሪካ ዳካር እስከ ምስራቅ ጅቡቲ ግዛቷን ለማስፋፋት ስታልም፣ እንግሊዝ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን እስከ ሰሜን ካይሮ ለመቆጣጠር በነበራት ፉክክር የፋሾዳው የጦርነት አፋፍ ተከሰተ።
የዚህ የፋሾዳው ፍጥጫ ቀጣይ ምዕራፍ፣ እንግሊዝ የውሃውን ዋስትና ለማረጋገጥ ስትል ኢትዮጵያን ለማዳከም ጣሊያንን በሞግዚትነት እንድትደግፍ እና የውጫሌን የክህደት ውል እንድታበረታታ አደረጋት። እንግሊዝና ግብጽ የውሃውን ፖለቲካ የሴራ ጥልቀት በማስፋት፣ ከዓመታት በኋላ የ1929 እና የ1959 ኢ-ፍትሃዊ የውሃ ስምምነቶችን በመፈረም የውሃውን ምንጭ ባለቤት ኢትዮጵያን ከገዛ ሀብቷ ለማግለል ሞከሩ። ሆኖም፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች ይህንን የቀኝ ገዥዎች ሴራ በዓድዋ ተራሮች ላይ ድባቅ መቱት።
የ40 ዓመታት የመርዝ ዘር እና የውስጥ ባንዳዎች
የሆነ ሆኖ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን የመበተን ሴራቸውን አላቆሙም። መላው አውሮፓ በዓድዋ ድል ተበሳጭቶ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ለ40 ዓመታት የመርዝ ዘር ሲዘራ ቆይቷል። ወራሪዎቹ የውሃውን ምንጭ ለመቆጣጠር ያደረጉት የቀጥታ ወረራ ሙከራ በጀግኖች ሲከሽፍ፣ ስልታቸውን በመቀየር በኢትዮጵያውያን መካከል የዘር፣ የቋንቋ እና የሃይማኖት ልዩነቶችን በማስፋት ሀገራችንን ከውስጥ ለማዳከም ሰፊ የሴራ ፖለቲካ ዘረጉ። በቅርብ ጊዜም ይህ የክፋት ሴራ በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት የኢትዮጵያን ኅልውና እስከመፈታተን ደርሶ ነበር። ታሪካዊ ጠላቶች የውስጥ ባንዳዎችን በገንዘብና መሳሪያ በመደገፍ ኢትዮጵያ ግድብ እንዳትገነባና ቀና እንዳትል ለማድረግ የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል።
ተበቃዩ ትውልድ፡- ከሕዳሴው ግድብ እስከ ቀይ ባሕር
ነገር ግን፣ የአሁኑ ትውልድ ይህንን የ100 ዓመታት አዙሪት ሰብሮ በመውጣት የሁለተኛውን ዓድዋ ድል በተግባር እያስመዘገበ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ሲይዙ፣ በውስጥ ተላላኪዎች የዝርፊያ ማዕከል ሆኖ የነበረውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በማስተካከል፣ ግድቡን ከሞት ታድገው፣ የካይሮንና የደጋፊዎቿን ዲፕሎማሲያዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎች ሁሉ ተቋቁመው ለታላቅ ክብርና ለመጠናቀቅ አብቅተውታል፡፡ የውሃ ፖለቲካው ሴራ በዚህ ታላቅ ትውልድ ክንድ ተሰበረ፤ ዓባይም በልጆቹ ላብ ተገደበ።
ይህ ትውልድ ያለፈውን ቁጭት የሚበቀለው አሮጌውን የመከፋፈል ፖሊሲ ‘በአብሮነት እና ሕብረ ብሔራዊነት ትርክት' በመተካት ነው። ታላቁ ትርክት ራሳችንን ከቅኝ ገዥዎች የጥላቻ ትርክት አላቆ፣ እርስ በእርስ ከመዳማት ወጥቶ፣ በመደመርና በሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ ሀገርን መገንባት ነው።
የሴራው ጥልቀት ዓባይን በመገደብ ብቻ አላበቃም። ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን የየብስ ቁልፍ ሰላቢ አድርገው ለማነቅ ያደረጉትን የረጅም ዘመን ጥረት በማክሸፍ፣ የዛሬው ትውልድ ዳግም ዓይኑን ወደ ቀይ ባሕር አዙሯል። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ የባሕር በሯን ለማስመለስና የባሕር ኃይሏን ዳግም ለማቋቋም የምታደርገው ስልታዊ እርምጃ፣ የፋሾዳውንም ሆነ የዘመናትን የካይሮን ሴራዎች ከስረ መሠረቱ የነቀለ ነው።
የፋሾዳውና የካይሮ ሴራዎች ዛሬም ያለፈውን በተበቀለው ትውልድ ከሽፈዋል። የግብጽና የእንግሊዝ የተጠላለፈ የውሃና የባሕር ፖለቲካ ሴራ እንዲሁም የፈረንሳይና የሌሎች ወራሪዎች የጥቅም ፉክክር ታሪክ በኢትዮጵያ ልዕልና ፊት ተንበርክኳል። የኢትዮጵያ ጠላቶች ምንም ያህል ቢዶልቱም፣ ሀገራችን በልጆቿ አንድነት የውሃውንም ሆነ የባሕር በሩን ፖለቲካ በአሸናፊነት እየተወጣች የነገዋን ታላቅ ኢትዮጵያ እውን ታደርጋለች!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: